ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የጎበኙ የውጭ አገር ቱሪስቶች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል - ኢዜአ አማርኛ
ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የጎበኙ የውጭ አገር ቱሪስቶች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል

ጎንደር፤ ሚያዚያ 21/2017(ኢዜአ)፦ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ባለፉት ዘጠኝ ወራት የጎበኙ የውጭ አገር ቱሪስቶች ቁጥር ከቀደመው በእጥፍ መጨመሩን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማሩ ቢያድግልኝ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ብሄራዊ ፓርኩንና በውስጡ የሚገኙ ብርቅየ እንስሳትን የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ የመጠበቅ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ፓርኩን የጎበኙ የውጭ አገር ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን የጠቆሙት ኃላፊው የጎብኚዎቹ ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ማደጉን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ፓርኩን ከተለያዩ የዓለም አገራት የመጡ 2 ሺህ 723 ቱሪስቶች እንደጎበኙት ገልፀዋል።
በፓርኩ አዋሳኝ ወረዳዎች በኢኮ ቱሪዝም የተደራጁ ማህበራትም ለቱሪስቶች የመጓጓዣ በቅሎ በማከራየት፣ ጓዝ በመጫን፣ መንገድ በመምራትና ምግብ በማብሰል 3 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ፓርኩ ከቱሪስቶች የመግቢያ ትኬትና ከፊልም ቀረጻ ስራ ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰብ እንደተቻለም ገልፀዋል፡፡
የፓርኩን ብዝሃ ህይወት የበለጠ ለመጠበቅና ብርቅዬ የዱር እንስሳቱን ከህገ-ወጥ አደን ለመታደግ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶች ወደ ትግበራ መገባቱን አመልክተዋል፡፡
ስትራቴጂክ ዕቅዱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የዱር እንስሳትን ህብረተሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ በአስተማማኝ መልኩ ለመጠበቅ የሚያስችል እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
በዚህም በፓርኩ ውስጥ ህገ-ወጥ አደን ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት መታየት መጀመሩንም ገልፀዋል።
የደባርቅ የኢኮ-ቱሪዝም ማህበራት ዩኒየን ስራ አስኪያጅ ቄስ ሞገስ አየነው በበኩላቸው፤ የውጭ አገር ቱሪስቶች ቁጥር መበራከት አባላቱን ከቱሪዝም ገቢ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡
ዩኒየኑ 8ሺህ አባላት ያሉት ሲሆን ለቱሪስቶች የመጓጓዣ በቅሎ በማከራየት፣ ጓዝ በመጫን፣ በማጀብና መንገድ በመምራት ከቱሪዝም አገልግሎቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንደ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የሌሎች ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ ሲሆን 412 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳለውም ይታወቃል።