በኢትዮጵያ ለተመቻቸልን የማህበራዊ አገልግሎት ምስጋናችን የላቀ ነው-ሱዳናዊያን ስደተኞች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለተመቻቸልን የማህበራዊ አገልግሎት ምስጋናችን የላቀ ነው-ሱዳናዊያን ስደተኞች
ገንዳ ውሃ፤ሚያዚያ 21/2017 (ኢዜአ) ፡-በኢትዮጵያ መንግስት ለተመቻቸልን የኢኮኖሚ፣የማህበራዊ አገልግሎትና የትምህርት እድል ምስጋናችን የላቀ ነው ሲሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን አፍጥጥ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሱዳናዊያን ስደተኞች ተናገሩ።
በሱዳን የተከሰተውን የእርስ በርስ ግጭት ተከትሎ በርካታ የሱዳን ስደተኞች ድንበር ተሻግረው የመጡ በመሆኑ ኢትዮጵያም ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞቹ በሰፈሩባቸው አካባቢዎች የኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ መሆኑም ይታወቃል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ አስተዳደር አፍጥጥ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከሚገኙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ሱዳናውያን ስደተኞች ለኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ከፍ ያለ ምስጋና እንዳላቸው ገልጸዋል።
ለሱዳናዊያን ኢትዮጵያ ሌላኛዋ ቤታችን ነች ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ በኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎት በመጠቀምና ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ የትምህርት እድልም ተመቻችቶልናል ብለዋል።
በመጠለያ ጣቢያው ከሚገኙት መካከል ተማሪ ሰዓዳ አብዱረህማን እና ተማሪ ሙሀመድ ኡስማን በኢትዮጵያ ለተመቻቸላቸው የትምህርት እድል አመስግነዋል።
በአፍጥጥ የስደተኞች መጠለያ በተገነባው ትምህርት ቤት በርካታ ወጣቶች የመማር እድል ማግኘታቸውን ጠቅሰው፥ በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ እውነተኛ ወዳጅነታቸውን አሳይተውናል ብለዋል።
በትምህርት ቤቱ የ6ኛ ክፍል ትምህርቷን እየተከታተለች ያለቸው ሰዓዳ አብዱረህማን፤ በመንግስት፣የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና የአካባቢው ማህበረሰብ እገዛ ብዙ ነገሮች እየተሟሉልን ነው ብላለች።
በጦርነቱ ሳቢያ ከሱዳን ትምህርቷን በማቋረጥ ወደ ኢትዮጵያ ብትመጣም በተመቻቸላት እድል ትምህርቷን እየተከታተለች መሆኑን ተናግራለች።
ሌላኛው የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሙሀመድ ኡስማን፤ በኢትዮጵያ በማህበራዊ አገልግሎት በተለይም በትምህርት ለተደረገልን ምቹ ሁኔታ ከፍተኛ ምስጋና አለን ብሏል።
በመጠለያው ከገባን ጀምሮ ሰብአዊ መብታችን ተከብሮ እንድንኖር ከማድረግ ባሻገር በተከፈተልን ትምህርት ቤት በቋንቋችን የመማር እድል አግኝተናል ፤ በማለት መደሰቱን ገልጿል።
ከሱዳን በስደት የመጡት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አብዱሰላም ሁሴን፤ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በችግር ወቅት የሱዳንን ዜጎች በመቀበል እያደረጉት ላለው በጎነት አመስግነዋል።
የሱዳንን ስደተኞች በመቀበልና ለትምህርት ቤት የግንባታ ቦታ በመስጠት ወጣቶች እንዲማሩ በማመቻቸት ያደረጉትን መልካምነት ታሪክ ሊዘነጋው የማይችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በስደተኞችና ስደት ተመላሾች አገልግሎት የአፍጥጥ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ደሳለኝ አስናቀ እንደተናገሩት፥ በአፍጥጥ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለስደተኞችና ለአካባቢው ማህበረሰብ ግልጋሎት የሚሰጡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ግንባታ ተከናውኗል።
ከግንባታውም ውስጥ አሁን አገልግሎት መስጠት የጀመረው ትምህርት ቤት ስደተኞችና የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆች እየተማሩበት እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪ ለስደተኞችና የአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጥ ጤና ጣቢያ እየተገነባ መሆኑንም አብራርተዋል።
በአማራ ክልል የምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አያና፤ ከተለያዩ አገራት የመጡ ስደተኞችን በመቀበል በመንግስት ድጋፍና እገዛ እየተደረገ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በተለይም ወጣቶችና ታዳጊዎች የመማር እድል እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፥ አሁን ላይ በአፍጥጥ የስደተኞች መጠለያ የተገነባው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል 900 የሱዳን ስደተኞች እና 501 ኢትዮጵያዊያን እየተማሩ መሆኑን ገልጸዋል።