ኢትዮጵያ እና የዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና የዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 21/2017 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ እና የዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች የኢትዮጵያን የእዳ አስተዳደር አስመልክቶ ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የዓለም ባንክ ግሩፕ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ መካሄዱ ይታወቃል።
በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ የዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ጋር ተወያይቷል።
ውይይቱ እ.አ.አ ማርች 2025 ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ በቡድን 20 አባል አገራት የዕዳ ማቃለያ ማዕቀፍ አማካኝነት በኢትዮጵያ የእዳ አስተዳደር ድርድር የተደረሰው ስምምነት ያለበት ደረጃ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
ሚኒስትሩ ለንግድ አበዳሪዎቹ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ሂደትን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
ልዑኩ ሁሉን አቀፍ ሪፎርሞቹን ተከትሎ ያለውን የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ አስመልክቶ ተወያይቷል።
ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያን የእዳ አስተዳደር አስመልክቶ የሚደረጉ ድርድሮች በተቀመጣላቸው ጊዜ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ መስማማታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።