የዓለም የእግር ኳስ አፍቃሪያን ዓይኖች ሁሉ ወደ ኤምሬትስ ያማትራሉ

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 21/2017 (ኢዜአ)፡- በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር አርሰናል እና ፒኤስጂ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ አርፎበታል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ በኤምሬትስ ይካሄዳል።

በሩብ ፍጻሜው አርሰናል የ15 ጊዜ የውድድሩን አሸናፊ ሪያል ማድሪድን በድንቅ ብቃት በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

ተጋጣሚው ፒኤስጂ በበኩሉ በአስቶንቪላ ቢፈተንም የመጨረሻ አራት ውስጥ ገብቷል። 

ሁለቱ ቡድኖች በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም በሻምፒዮንስ ሊጉ ተገናኝተው አርሰናል በቡካዮ ሳካ እና ካይ ሃቫርትዝ ግቦች 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ቡድኖቹ እ.አ.አ 2016/17 በምድብ ደረጃ ተገናኝተው ሁለት ጊዜ ሳይሸናነፉ አቻ ተለያይተዋል። 


የለንደን እና የፓሪስ ከተማ ክለቦቹ በዛሬው ጨዋታ ተመጣጣኝ እና ለተመልካች አዝናኝ ፉክክር ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል።


የ45 ዓመቱ ስሎቬኒያዊ ስላቫኮ ቪንቺች ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።


በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ባርሴሎና ከኢንተር ሚላን ነገ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም