ዕውቀት፣ ሃብት፣ ሰውና ብሩህነት ከተስማሙ ኢትዮጵያን ፈጥኖ ወደ እድገት ማማ ማስፈንጠር ይቻላል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ዕውቀት፣ ሃብት፣ ሰውና ብሩህነት ከተስማሙ ኢትዮጵያን ፈጥኖ ወደ እድገት ማማ ማስፈንጠር ይቻላል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2017(ኢዜአ)፦ዕውቀት፣ ሃብት፣ ሰውና ብሩህነት ከተስማሙ ኢትዮጵያን ፈጥኖ ወደ እድገት ማማ ማስፈንጠር እንደሚቻል የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
"ኑ ጎንደርን እንሞሽር" ለጎንደር ከተማ የልማት ስራዎች የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ሸራተን አዲስ ሆቴል ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ፣ የፌዴራልና የክልሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚሁ ጊዜ፥ በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ የተገኘሁት በልማት ተግባር የተጉና የበረቱትን ለማመስገን ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማት እጅግ ትልቅ ሃሳብ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፥ ድርጊቱም የከተሞችን ዕድገት መሰረት በማስያዝ የህዝብን ኑሮ የሚያሻሽል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች በዕውቀትና ሃብት ዕድገታቸውን በማሳለጥ ከዓለም ስልጣኔ ጋር መዋሃድ እንደሚኖርባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የከተሞችን የዕድገት ሰልፍ በማሳመር ወደፊት መትጋት እንደሚገባ ጠቁመው፥ የኢትዮጵያ ከተሞች እጣ ፈንታ መሰልጠንና መሰልጠን ብቻ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮሪደር ልማት ሲያስቡ የሌሎች ዓለማት ከተሞችን ዕድገት በማሰብ መሆኑን አስረድተዋል።
የዓድዋ ሙዚየምን ዕፁብ ድንቅ ስራ ሲሉ የገለጹት ፕሬዚዳንት ታዬ፥ ዕውቀት፣ ሃብት፣ ሰውና ብሩህነት ከተስማሙ ኢትዮጵያን ፈጥኖ ወደ እድገት ማማ ማስፈንጠር ይቻላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ኃያል ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፥ አሁን ሰርቶ የማሳየትና የመገለጥ ዘመን በመሆኑ በልማት ጎዳና መገስገስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ጎንደር የጋራ የኢትዮጵያዊያን የእጅ ስራ ናት ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፥ የከተማዋ ገናና ታሪክም እንደ አዲስ የሚነገር ሃሳብ ሳይሆን በጋራ የተገነባ ነው ብለዋል።
መፍረስን ለማዳን ብሩህነትን ይጠይቃል ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጎንደር ከተማ ልማት ለወሰዱት ወሳኝ እርምጃ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ጎንደርን የልማት ማዕከል በማድረግ ህዝብን ከድህነት የማውጣት ቁልፍ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።