ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አካታች የኢንዱስትሪ ልማትና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 20/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ አካታች የኢንዱስትሪ ልማት እና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ እየሰራች እንደምትገኝ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ ገለጹ።

3ኛው የኢራን-አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ኮንፈረንስ በቴህራን እየተካሄደ ይገኛል።

በኮንፈረንሱ “ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን እና የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተካሄዷል።

ሚኒስትር ዴኤታው በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ አካታች የኢንዲስትሪ ልማትን ለማምጣትና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ እያከናወነች ያለውን የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች በሚመለከት ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ተሞክሮዎችንም አጋርተዋል።

በኢትዮጵያ እየተተገበረ ባለው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚና የፖሊሲ ማሻሻያ አማካኝነት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የማበረታቻ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት አጠቃላይ የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት አካባቢዎችን ለማሻሻልና ለዘርፉ ተዋናዮች ምቹ ለማድረግ በቁርጠኝት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ሳቢ የንግድና ኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር የኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣የገንዘብ ፖሊሲ፣ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት እና ኢኮኖሚውን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ነው ያብራሩት።

የተወሰዱት ጥልቅ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለውጭ ባለሀብቶች መልካም እድል መፍጠራቸውን ገልፀው፣ የኢራን ባለሀብቶች ግብርና ማቀነባበሪያና ኢንዱስትሪ ልማትን ጨምሮ የማኑፋክቸሪንግ ና የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢነርጂና ታዳሽ ኃይል ልማት፣ በምህንድስና በቴክኖሎጂ እንዲሁም የእውቀት ሽግግር እና መሠረተ ልማት መስኮች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ከስብስባው ጎን ከኢራን የኢንዱስትሪ፣ ማዕድንና ንግድ ሚኒስትር ሬዛ ፋቴሚ አሚን እና ከኢራን የግብርና ሚኒስትር ጎላምሬዛ ኑሪ ጌዜልጄህ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ሀገራቱ በግብርና ሜካናይዜሽን፣ በማዳበሪያ እና በአቅም ግንባታ ዘርፎች በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም