የጎንደርን ቅርስ ከመጠበቅ ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ በታሪኳ ልክ የደመቀች ከተማ ለማስረከብ እየተሰራ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደርን ቅርስ ከመጠበቅ ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ በታሪኳ ልክ የደመቀች ከተማ ለማስረከብ እየተሰራ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2017(ኢዜአ)፦ የጎንደርን ቅርስ ከመጠበቅ ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ በታሪኳ ልክ የደመቀች ከተማ ማስረከብ የሚያስችሉ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።
ለጎንደር ከተማ የልማት ስራዎች የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር "ኑ ጎንደርን እንሞሽር" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ከተማ ሸራተን አዲስ ሆቴል ተካሒዷል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ፣ የፌዴራልና የክልሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት የታሪክ አሻራ ለሆነችው የጎንደር ከተማ የገቢ ማሰባሰቢያ ለመታደም ለመጡ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ለዘመናት ቀደምት የስልጣኔ ፋና ወጊ የሆነችው ጎንደር ከተማ ታሪካዊ ቅርሶቿ መታደሳቸውን ጠቁመው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጎንደር ከተማ የተከናወኑ የልማት ተግባራት በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ደስታና አድናቆት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በስልጣኔ ያጌጠ አሻራውን ጠብቆ ተጨማሪ ልማትን በመገንባት ለኑሮና ኢንቨስትመንት ምቹ ከተማን ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የዘመናት ጥያቄ ሆነው የቆዩ የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ እና ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር ሰጭነት የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስታት የዕድሳት ስራን ጨምሮ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው ይታወሳል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ የጎንደር ኮሪደር ልማት መጠናቀቁንና 12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው ሁለተኛው ምዕራፍ መጀመሩም ይታወቃል።