የዓለም ስርዓት በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት እኩል ውክልናን በሚያረጋግጥ መልኩ ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ስርዓት በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት እኩል ውክልናን በሚያረጋግጥ መልኩ ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2017(ኢዜአ)፡- የዓለም የአስተዳደር ስርዓት በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት እኩል ውክልናን በሚያረጋግጥ መልኩ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) አመለከቱ።
የባለብዝሃ ወገን የዲፕሎማሲ ማዕቀፍ መጠናከር ለሪፎርሙ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
የ2025 የመጀመሪያው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ዛሬ በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ መካሄድ ጀምሯል።
በውይይቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) እየተሳተፉ ነው።
የሚኒስትሮቹ ስብሰባ መክፈቻ ላይ “ብሪክስ የዓለም እና ቀጣናዊ ቀውሶችን ለመፍታት ያለው ሚና፣ ለሰላም እና ደህንነት መረጋጋጥ የሚያስችሉ መንገዶችን ማጠናከር” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ውይይት ተካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በውይይቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ለብዝሃ ወገን ትብብር እና የጋራ ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የዓለም አስተዳደር ስርዓት ላይ ማሻሻያ በማድረግ አፍሪካን ጨምሮ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በእኩልነት የሚወከሉበት ስርዓት መፍጠር እንደሚገባም አመልክተዋል።
የዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፎርም አንኳር ትኩረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባለብዝሃ ወገን ማዕቀፍ ማጠናከር ላይ መሰረት ያደረገ መሆን አለበት ነው ያሉት።
ሚኒስትሩ በዓለም ላይ ያሉ ውጥረቶችን አስመልክቶ ሀሳባቸውን ያነሱ ሲሆን የብሪክስ ሀገራት ቀውሶቹ በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ እንዲፈቱ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የደቡብ ንፍቀ ዓለምን የደህንነት፣ የኢኮኖሚ እና አጠቃላይ ፍላጎቶችን የሚያስጠብቁ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር የጋራ የሚኒስትሮች የአቋም መግለጫን እንደሚያወጣ ይጠበቃል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከስብሰባው ጎን ለጎን ከብሪክስ አባል ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን እንደሚያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።