ሰላም ሚኒስቴር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነትና አብሮነትን ለማጠናከር እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ሰላም ሚኒስቴር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነትና አብሮነትን ለማጠናከር እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2017(ኢዜአ)፦ ሰላም ሚኒስቴር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነትና አብሮነትን ለማጠናከር እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው የሰላም ሚኒስቴርን የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።
ቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው ግብረ መልስ እንዳስታወቀው፤ ሚኒስቴሩ የፌዴራልና የክልል መንግስታትን እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የሰራቸው ስራዎች የሚደነቁ ናቸው።
ሚኒስቴሩ በሀገር ግንባታና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ሊሂቃን ሊያበረክቱት በሚገባ ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ መድረሱን ተጠቁሟል።
የአጋርና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማጠናከር ሚኒስቴሩ እየሰራ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሞ፤ ሀገራዊ አንድነትንና አብሮነትን ለማጎልበት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መስራቱን አብራርቷል።
ሚኒስቴሩ የተቋሙን ሪፎርም ስራዎች እያከናወነ መሆኑና የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓትን በመዘርጋት በጀት በአግባቡ መጠቀሙም ተመልክቷል።
የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ የዘጠኝ ወር ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከክልሎች ጋር በመተባበር የተሰራው ስራ ውጤት አስገኝቷል።
ለአብነትም በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በቅንጅት የተሰራው ስራ ያስመዘገበውን ስኬታማ ውጤት አንስተዋል።
ሚኒስቴሩ ብሄራዊ ጥቅም፣ ማንነት፣ ዕሴትና ዘመኑን የዋጀ አርበኝነት ላይ ያተኮሩ አራት ሰነዶች ማዳበር መቻሉን አመልክተዋል።
እስከ አሁን በ12 ዙር ከ80ሺህ በላይ የሰላም በጎ ፍቃድ ወጣቶችን በማሰማራት ወጣቶች ህብረ ብሄራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ የተለያዩ ስራዎች ማከናወኑም አብራርተዋል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላት ባቀረቡት ጥያቄና አስተያየት፤ ሚኒስቴሩ ዘላቂ የልማት ግቦች ከሰላም ግንባታ ጋር ለማስተሳሰርና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጎልበት በበጎ ፈቃደኞች በተሰሩ ስራዎች ምን ውጤቶችን እንዳስመዘገበ ጠይቀዋል።
የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ሚኒስቴሩ ብሄራዊ የበጎ ፈቃድ ወጣቶችን በማሰማራት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልዩነቶችን ለመፍታት እንዲሁም ለማረም ሀገራዊ ምክክር የኮሚሽንና የሽግግር ፍትህ በኩል ትልልቅ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር) ሚኒስቴሩ የፌዴራልና የክልል መንግስታትን ግንኙነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር የሰራው ስራ የሚበረታታ ነው።
የብሄራዊ በጎ ፍቃድ ወጣቶችን በማሰማራት እንዲሁም የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመን የሰራው ስራ አበረታች መሆኑንም ጠቁመዋል።
ህብረ ብሄራዊ አንድነትና አብሮነትን ለማጠናከር እንዲሁም የቅድመ ግጭት ትንበያ ላይ በጥናት ላይ ተመስርቶ ያከናወነው ስራም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ(ዶ/ር) በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ማስፈን የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎች ማከናወኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የፌዴራሊዝም ስርዓትን ለማጠናከርና ግጭቶችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ አበረታች ስራዎች ማከናወኑንም ተናግረዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ሚኒስቴሩ የግጭት መከላከልና መከታተያ ቴክኖሎጂ ተደራሽ እንዲሆንና ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶችን ለማስቀጠል በትኩረት እንዲሰራ ጠይቋል።