ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የአጋርነት ትብብሯን እያጠናከረች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የአጋርነት ትብብሯን እያጠናከረች ነው

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 20/2017 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከአጋሮች ጋር ያላትን የጋራ ትብብር በማጠናከር ላይ እንደምትገኝ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፈረንሳይ እና ከሱዳን ምሁራን ጋር የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ስርዓትን ለማጎልበት የሚያስችል አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።
ከኢትዮጵያ፣ ከፈረንሳይ እና ከሱዳን የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች በአውደ ጥናቱ ላይ ተሳትፈዋል።
አውደ ጥናቱ በኢትዮጵያ፣ በፈረንሳይ እና በሱዳን ምሁራኖች መካከል በትምህርት፣ በኢኖቬሽን፣ በቴክኖሎጂ፣ በዲጂታል እውቀት እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ በጋራ መስራትን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚያስችሉ የትምህርት ጉዳዮች ዘርፍ ላይ ከአፍሪካ እና ከሌሎች አጋር ዓለም ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራች ነው ብለዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማጎልበት የሚካሄደው አውደ ጥናት ለሀገራቱ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።
በሱዳን የፈረንሳይ አምሳደር እና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በርትራንድ ኮቼሪ በሀገራቱ ዘመኑ የሚሻውን ቴክኖሎጂ ለማስታጠቅ፣ ወጣቶች የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ክህሎት እና እውቀት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን መተግበር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ኤል ዛይን ኢብራሂም ሁሴን አውደ ጥናቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን የትብብር ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ጠቃሜታ አለው ብለዋል።
አውደ ጥናቱ ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።