ኢትዮጵያ አካታች የትምህርት ስርዓት ሪፎርም በማድረግ ተጨባጭ ውጤት አምጥታለች - ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አካታች የትምህርት ስርዓት ሪፎርም በማድረግ ተጨባጭ ውጤት አምጥታለች - ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አካታች የትምህርት ስርዓት ሪፎርም በማድረግ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
"ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025" የአፍሪካ የትምህርት፣ አይ ሲ ቲ እና ክህሎት የሚኒስትሮች ስብሰባ "በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን ማስተማርና ማብቃት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።
ጉባኤው የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ በሪፎርም፣ አቅም ግንባታ የቴክኖሎጂ ስትራቴጂካዊ ትብብር በመፍጠር የአፍሪካን የትምህርት ተደራሽነት ማስፋት ያለመ ነው።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት 2024ን የትምህርት ዓመት ብሎ መሰየሙን ተከትሎ ገቢራዊ ለማድረግ ያከናወነችውን ተግባር በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ስያሜ አምስት ዓመት ቀደም ብላ ሥራ መጀመሯን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተደረገው ሀገራዊ ሪፎርም የትምህርት ዘርፉን አካታችነት ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት እኩል የሚስተናገዱበት ነው ብለዋል፡፡
ከለውጡ በፊት የትምህርት ጥራት ችግር እንደነበር ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የቅድመ መደበኛ ትምህርት የከተማ ነዋሪዎች ብቻ ተደርጎ ይወሰድ እንደነበርም አንስተዋል፡፡
በትምህርት ተቋማት ይሄን ያህል መጠን ያለው የሰው ኃይል አፈራን ከሚለው ውጭ ምን ያህል ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ነው የሚለው ሊያሳስበን ይገባል ብለዋል፡፡
በዚህም በትምህርት ዘርፉ በተደረገው ሪፎርም የቅድመ መደበኛ ትምህርትን በማስፋፋት ጥራትና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ35 ሺህ በላይ የትምህርት መሰረተ ልማት የተሟላላቸው የቅደመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
በከተማም ሆነ በገጠር ለተማሪዎች በቂ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የህብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ትምህርት ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚሸፈን አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ የሀብት ማሰባሰብ በሁሉም ዜጋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያውያንና በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የትምህርት መሰረተ ልማትን ከመገንባት ባለፈ የመምህራንን አቅም መገንባት ይገባል ብለዋል፡፡
የዩጋንዳ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ጆይሲ ካዱኩ(ዶ/ር) በዩጋንዳ 29 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ከ18 እስከ 38 ዓመት የእድሜ ክልል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከአፍሪካም አልፎ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ወጣቶችን ለማፍራት ምቹ የትምህርት ሥነ ምህዳር መፈጠሩን ገልጸው፤ ዲጂታላይዜሽን እና አይ ሲ ቲ በትምህርት ሥርዓቱ ለማካተት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዲጂታል ትምህርትን ማስፋፋት የሀገሪቱ ብሔራዊ የልማት እቅድ አካል መሆኑን ገልጸው፤ በገጠርና በከተማ ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የኦን ላይን የትምህርት ስርዓት ገቢራዊ አድርጓል ብለዋል፡፡
የስዋቲኒ ትምህርትና ስልጠና ሚኒስትር ኦውን ዙማሎ፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህራንን አቅም መግንባት እና ዲጂታል ቴክኖሎጂን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ስዋቲኒ በትምህር ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ዜጎችን ማፍራት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ማድረጓንም ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ብዙ ሰርተናል፤ የትምህርት ሥርዓቱን ለመለወጥም ብዙ ጥረት አድርገናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡