የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃና ምዝገባን ከሰባት ሺህ በላይ ለማሳደግ እየተሰራ ነው -የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃና ምዝገባን ከሰባት ሺህ በላይ ለማሳደግ እየተሰራ ነው -የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 20/2017(ኢዜአ)፦የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃና ምዝገባን በዘንድሮው ዓመት ወደ ሰባት ሺህ 5 መቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ለ23ኛ ግዜ የሚከበረው የዓለም አቀፍ የአእምሯዊ ንብረት ቀን በተለያዩ መርሀ ግብሮች መከበር ጀምሯል።
እለቱን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል እንደገለፁት የፈጠራ ስራ ውጤቶች ለአገር ገፅታ ግንባታ፣ ለስራ እድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ መስፋፋት ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው።
ከፈጠራ ስራ ዘርፎች መካከል የሙዚቃ ፈጠራ ስራ በሁሉም መስክ ለሚከናወኑ ተግባራት አጋዥ መሳሪያ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ብዙ ባህል፣ እሴትና ትውፊት ያላት አገር መሆኗ ደግሞ ለሙዚቃ ፈጠራ ስራ መጎልበት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።
መንግስት የሙዚቃና መሠል የፈጠራ ስራዎች እንዲጠበቁና ለአገር ያላቸውን ፋይዳ ይበልጥ እንዲያጎሉ የሚያስችሉ የአሰራር ስርዓቶች እየዘረጋ መሆኑንም አብራርተዋል።
በዚህ ረገድ ባለስልጣኑ የአገራትን ተሞክሮ በመቀመር፣ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከርና የምዝገባና መሰል አሰራሮችን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ዋና ዳይሬክተር እንደገለጹት የፈጠራ ስራን ከማበረታታ በዘለለ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ለማጉላት ምቹ እድልን እየፈጠረ ይገኛል።
ለአብነትም ባለፈው አንድ አመት ብቻ ከ5 ሺህ በላይ የምዝገባና የጥበቃ ስራ ማከናወን ማቻሉን ገልጸው በዘንድሮው አመትም ወደ 7 ሺህ 5 መቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን፣ ተደራሽነቱን ለማስፋትና የፈጠራ ሰራ ባለሙያዎች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑን አክለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው የቴክኖሎጂ እድገትን ለማረጋገጥ የፈጠራ ስራ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ተናግረዋል።
የአእምሯዊ ንብረት መብት እና የቅጅ መብት ስራዎችን ለማስጠበቅ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ህጋዊ አሰራር በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ ረገድ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና የፈጠራ ስራዎች ለአገር ልማትና ለዜጎች አብሮነት የድርሻቸውን እንዲወጡ በማድረግ ረገድ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የመብት ማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የፈጠራ ስራ ውጤቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ለማጉላት በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፈጠራ ውጤቶች አውደርዕይ የተከፈተ ሲሆን የበዓሉ ተሳታፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች አውደ ርዕዩን ጎብኝተውታል።
የዘንድሮው አለም አቀፍ የአእምሯዊ ንብረት ቀን "ሙዚቃና አእምሯዊ ንብረት ፤ ፈጠራን ማጎልበት/ ማፍጠን'' በሚል መሪ ሀሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተለያዩ ሁነቶች የሚከበር መሆኑም ተገልጿል።