መዲናዋን ሰላማዊ፣ የተረጋጋች እና ለመኖር ምቹ ማድረግ የሚያስችሉ ውጤታማ የፀጥታ ስራዎች ተከናውነዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
መዲናዋን ሰላማዊ፣ የተረጋጋች እና ለመኖር ምቹ ማድረግ የሚያስችሉ ውጤታማ የፀጥታ ስራዎች ተከናውነዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2017(ኢዜአ)፡- አዲስ አበባን ሰላማዊ፣ የተረጋጋች እና ለመኖር ምቹ ማድረግ የሚያስችሉ ውጤታማ የፀጥታ ስራዎች መከናወናቸውን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዘጠኝ ወራት የፀጥታ ስራዎችን ገምግመዋል።
በግምገማው ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተገኝተዋል።
ከንቲባዋ የከተማዋን እድገት እና ለውጦች የሚመጥን የፀጥታ መዋቅር ማደራጀት፣ ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የፀጥታ ስጋት ሊሆን የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን ቀድሞ በመለየትና ህዝቡን በቀጥታ በማሳተፍ የሰላሙ ባለቤት እንዲሆን በተከናወኑ ስራዎች ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ወንጀል በመከላከል፣ ተጠርጣሪዎችን አድኖ በመያዝ በመመርመርና በማስቀጣት ከተማዋን ሰላማዊ፣ የተረጋጋች እና ለመኖር ምቹ በማድረግ ረገድ ውጤቶች መገኘታቸውንም አመልክተዋል።
በግምግማው ላይ የፀጥታ መዋቅሩ የከተማ አስተዳደሩ ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሆናቸው መናገራቸውን አመልክተዋል።
በከተማዋ የወንጀል መከላከል እና የመቆጣጠር አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ የከተማው ነዋሪዎች በሰላም ሰራዊት በመደራጀት ያበረከተዉ የላቀ አስተዋፅኦ፣ የሰላም እና የፀጥታ መዋቅር፣ የፓሊስ ኃይል፣ ደንብ ማስከበር እና ሌሎች የፌደራል ፀጥታ አካላት ጋር የመስራቱ ውጤት እንደሆነም በማንሳት።
ከንቲባዋ መዲናዋን ከተደራጀ የዝርፊያ፣ ሌብነት፣ ንጥቂያ እና ከየትኛውም የፀጥታ ስጋት የፀዳች በማድረግ፣ ተቋማዊ ብቃት በማሳደግ፣ የሪፎርም ስራን በማጠናከር፣ የአገልጋይነት ስነምግባር በመላበስ ህብረተሰቡን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በብቃት ማሳተፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የሰላም ሰራዊት እና የደንብ ማስከበር አባላት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን ይበልጥ በማጠናከር የተገኙ ለውጦችን አጠናክረው እንዲሰሩ ማሳሰባቸውንም የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።