በአማራ ክልል የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታት እድገትን ለማፋጠን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታት እድገትን ለማፋጠን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ደሴ ፤ ሚያዚያ 20/2017(ኢዜአ)፡ -በአማራ ክልል የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎችን በመደገፍና በማበረታታት እድገትን ለማፋጠን የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) ገለጹ።
የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ የሰራቸውን ማሽኖች የርክክብ ሥነ- ሥርዓት ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።
ከክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ ጋር በተከናወነው የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) እንደተናገሩት ፤ በክልሉ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቷል።
በተለይ ተቋማት አሰራራቸውን በቴክኖሎጂ በማዘመን ተገልጋዩ ህብረተሰብ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለፈጠራና ለቴክኖሎጂ ስራዎች ደግሞ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በማበረታታት የወጣቶችን እውቀትና ክህሎት ማሳደግ ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የክልሉ የልማት ድርጅቶች አካል የሆነው የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝን በመደገፍና የገበያ ትስስር በመፍጠር ሥራውን እንዲያዘምንም እንዲሁ።
የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘላለም በላይ በበኩላቸው፤ ኢንተርፕራይዙ የኢንዱስትሪና የግብርና መገልገያ ማሽኖችን በማምረት ለተጠቃሚዎች እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ የታገዙ ማሽኖችን በመፍጠር፣ በማላመድና በማስፋት ላይ በማተኮር የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በኢንተርፕራይዙ የተሰሩ 117 የእንጨት መሰንጠቂያ፣ የበቆሎ መፈልፈያ፣ ሞተርና ሌሎችንም ማሽኖችን አሻሽሎ በመስራት ዛሬ ለክልሉ ሥራና ስልጠና ቢሮ ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።
ማሽኖቹ ተግባር ተኮር ሥልጠናን የሚያጠናክሩ፣ የኢንዱስትሪና የግብርና ሥራዎችን የሚያዘምኑ በመሆናቸው ተፈላጊ ናቸው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ስቡህ ገበያው ናቸው።
የተረከቧቸውን ማሽኖች ለተለያዩ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በማከፋፈል ፈጥነው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊና የኢንተርፕራይዙ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ጥላሁን መሀሪ፤ ኢንተርፕራይዙ ዘመኑን የዋጀ የተሻለ አሰራር እንዲኖረው ድጋፍ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ፤ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።