በክልሉ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ፈጥነው ህብረተሰቡ ጋር እንዲደርሱ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው - አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ፈጥነው ህብረተሰቡ ጋር እንዲደርሱ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው - አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን

አዳማ፤ ሚያዝያ 20/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ፈጥነው ህብረተሰቡ ጋር እንዲደርሱ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን ገለጹ።
6ኛው ዙር የኦሮሚያ የፈጠራ፤ ቴክኖሎጂና የንግድ ስራ ክህሎት ውድድርና አውደ ርዕይ በጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረህማንና በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ከተሞች ክላስተር አስተባባሪ አቶ መስፍን መላኩ ተከፍቷል።
በወቅቱ አፈ ጉባኤዋ እንደገለፁት ወጣቶች ቴክኖሎጂን በማላመድ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ የፈጠራ ውጤቶች ማውጣት አለባቸው።
በተለይ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ግኝቶችና ውጤቶች ፈጥነው ህብረተሰቡ ዘንድ በስፋትና በተሻለ ጥራት እንዲደርሱ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሰርቶ የመለወጥ እሳቤ እንዲጎለብት፤ በክህሎትና በቴክኖሎጂ ፈጠራ የበቁ ወጣቶችን ከማፍራት አኳያ በተሻለ ፍጥነት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶች በልፅገው ወደ ልማቱ እንዲገቡ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በምክትል ፕሬዘዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ክላስተር አስተባባሪ አቶ መስፍን መላኩ በበኩላቸው በተቋማቱና በፈጠራ ባለቤቶች የወጡ ቴክኖሎጂዎች የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየፈቱ መሆናቸው ተናግረዋል።
በተለይ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች በክህሎትና በስራ ፈጠራ ላይ እየሰሩ ያሉት የፈጠራና ቴክኖሎጂ ልማት ስራዎች የብልፅግናን ጉዞ ለማሳካት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
የማኑፋክቸሪንግና የጎጆ ኢንዱስትሪን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር 'ሲንቄ ሊዝ ማሽን ኢንሼቲቭ' የተሰኘ መጀመሩን ጠቅሰው ይህም የፈጠራና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማበልፀግ ከውጭ የሚገቡ ማሽኖችን መተካት አስችሏል ብለዋል።
በፈጠራ የወጡ ቴክኖሎጂዎች ውጤቶች ለምተው በስፋት ለአርሶ አደሩና ለከተማው ህብረተሰብ እንዲቀርቡ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ቴክኖሎጂን በመቅዳትና በማላመድ የክልሉ ኮሌጆች በተሻለ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኤባ ገርባ ናቸው።
ወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል የኢንተርፕርነርሽፕ፤ የክህሎትና የንግድ ስራ ፈጠራ ላይ በስፋት እንዲሳተፉ በአቅም ግንባታና በሰርቶ ማሳያ ጭምር ከፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በውድድሩና አውደ ርዕዩ በ21 የውድድር አይነቶች በክህሎት፤ በቴክኖሎጂ፤ በንግድ ስራ ፈጠራና በቴክኖሎጂ ምርምር 400 የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።