ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነው - የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚደነቅ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እየተከናወኑ የሚገኙ የለውጥ ስራዎችን ተመልክተዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በዲጂታል የመረጃ ተደራሽነት አማራጮች ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ድምፅ ለመሆን የጀመራቸውን ሥራዎች በማስመልከትም ለቋሚ ኮሚቴው ገለፃ ተደርጓል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንደሞ፤ በምክር ቤቱ የሚወጡ ሕግጋት በትክክል ከተተገበሩ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) ማሳያ ነው ብለዋል።

የመገናኛ ብዙኅን የሥራ ባህሪን ታሳቢ ያደረጉ ሕግጋት፣ ደንቦችና መመሪያዎች በአግባቡ ከተፈጸሙ ውጤት እንደሚያመጡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የሰራተኞች መመሪያን በማሳያነት ገልጸዋል።

ጠንካራ የመገናኛ ብዙኃን የሌለው ሀገር ተሰሚነት አይኖረውም ያሉት አቶ አዝመራው፤ በዚህም ከራስ አልፎ ለሌሎችም ልሳን የሚሆን ተደማጭ መገናኛ ብዙኅን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከዚህ ቀደም የነበሩበትን ችግሮች በመፍታት የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እያስመዘገበ ላለው ስኬት በትጋት እየሰሩ ለሚገኙ የተቋሙ የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞችም ምስጋና አቅርበዋል።


 

የቋሚ ኮሚቴው አባል አቡኒ ዓለም፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሀገር አልፎ የአፍሪካን ጥቅም ለማስከበር እየሰራቸው የሚገኙ የመረጃ ተደራሽነት ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢዜአ በቴክኖሎጂና የሰው ሃይል በመታገዝ መረጃን በጥራትና በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ተልዕኮውን እየተወጣ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ የቋሚ ኮሚቴው አባል መርዲያ አማን ናቸው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋማትን የስራ ባህሪያት ታሳቢ በማድረግ የሚወጡ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቶች በትክክል እየተተገበሩ እንደሚገኝ ኢዜአ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ ኢዜአ ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር፣ ሀገራዊ ገጽታን የመገንባትና የአፍሪካ ድምጽ የመሆን ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ያወጣው የሕግ ማዕቀፍ ኢዜአ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ ማስቻሉን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም