የደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ ቤተ መንግስት የጥገናና የመልሶ ማልማት ስራ ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ ቤተ መንግስት የጥገናና የመልሶ ማልማት ስራ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 20/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ ቤተመንግስት የጥገናና የመልሶ ማልማት ስራ ለማከናወን ከቢዋይ ኤም ቲ ኮንትራክተር ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል።
ደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ በከሬ ከ1881 ዓ.ም እስከ 1916 ዓ.ም ድረስ የቀድሞ ወለጋ ጠቅላይ ግዛትን አስተዳድረዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ጥንታዊው እና ታሪካዊው ቤተ መንግሥት ለረዥም ዓመታት እድሳት ሳይደረግለት እና በቱሪዝሙ ዘርፍ አገልግሎት ሳይሰጥ ቆይቷል።
ቅርሱ ከጥንት የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተያያዙ ስፍራዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከተመረጡ ስፍራዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጥገናው ቅርሱ የነበረውን አሻራና ይዘት በጠበቀ መልኩ የቅርስ ጥገና መርሆዎችን በተከተለ መንገድ በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።
ጥገናው በተያዘለት የሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ጥራቱን ጠብቆ መጠገንና ለሃገር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መሆን እንዳለበትም ነው የገለጹት።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ በበኩላቸው የቤተመንግስቱ እንዲሁም የምድረ ግቢው ጥገና በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
የቢዋይ ኤም ቲዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በዛብህ መለሰ የታሪካዊውን ቤተ-መንግስት ጥገና በተፈለገው ጊዜና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ በከሬ ከ1881 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1916 ዓ.ም. ድረስ የቀድሞ ወለጋ ጠቅላይ ግዛትን ያስተዳድሩ እንደነበር የባለስልጣኑ መረጃ ያመለክታል።
ቤተ መንግስቱ ከአዲስ አበባ በስተ-ምዕራብ በኩል 319 ኪሎ ሜትር ርቀት ነቀምቴ ከተማ የሚገኝ ነው።
ንጉሱ ቤተ መንግስታቸውን የመሰረቱት 1830 ዓ.ም ሲሆን ቤተመንግስቱ ያረፈበት ቦታ ስፋቱ 2 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት እንደሚያካልል የባለስልጣኑ መረጃ ያመላክታል።