በፈጠራ ሥራችን ሀገራዊ ልማትን ለሚያግዙና ከውጭ የሚገቡትን ለሚተኩ ምርቶች ትኩረት ሰጥተናል - የፈጠራ ባለቤቶች

ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 20/2017(ኢዜአ)፦ በፈጠራ ሥራቸው ሀገራዊ ልማትን ለሚያግዙና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ትኩረት መስጠታቸውን በሲዳማ ክልል የፈጠራ ባለቤቶች ገለጹ።

የሲዳማ ክልል ሥራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በበኩሉ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን ለማበረታታትና ምርቶቻቸውን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የክልሉ የቴክኖሎጂ ክህሎትና የጥናትና ምርምር አውደ ርዕይና ውድድር "ብሩህ አዕምሮዎች የተፍታቱ እጆች በክህሎት የበቁ ዜጎች" በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።

በውድድሩ የፈጠራ ሥራቸውን ይዘው ከቀረቡት መካከል የሀዌላ ቱላ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ መምህር ሀብታሙ ዘካሪያስ በአንድ ጊዜ አራት ሰዎችን የሚያጓጉዝ ብስከሌት ይዞ መቅረቡን ተናግሯል።

የፈጠራ ስራው በሀዋሳ ከተማ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለውን የኮሪደርና አረንጓዴ ልማት ታሳቢ ማድረጉን ጠቁሞ፣ ሳይክሉን በአንድ ጊዜ አራት ሰዎች የሚያሽከረክሩት መሆኑን ገልጿል።

ምርቱ ከውጭ ይገባ የነበረውን ሳይክል የሚተካና በተሻለ ዋጋ መቅረቡን ገልጾ፣ በአንድ ጊዜ አራት ሰዎችን ማሳፈሩ በኮሪደር መንገድ ላይ ሰዎች እየተዝናኑ መጓጓዝ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ከሀዋሳ ተግባረ ዕድ ቴክኒክ ኮሌጅ መምህር ተካልኝ ተሻለ በበኩላቸው አነስተኛ የክብደት ማንሻ ወይም የክሬን ተሽከርካሪ መስራታቸውን ገልጸዋል።

የፈጠራ ሥራውን በሀዋሳ ከተማ ከጽዳት ሥራ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር መነሻ በማድረግ መስራታቸውንም ነው የተናገሩት።

በቀላል የኤሌክትሪክ ሃይል የእህል መፍጫ ማሽን የሰራው ደግሞ በሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የደረጃ 3 ተማሪ ይስማ ዎያሞ፣ የፈጠራ ውጤቱ በገጠር በሴቶች ላይ በድንጋይ ወፍጮ ሲደርስባቸው የነበረውን ጫና የሚያቃልል መሆኑን ተናግሯል።

የሲዳማ ክልል ሥራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፍስሃ ፍቾላ በቴክኖሎጂ ፈጠራ የተሰማሩትን የመደገፍና የማብቃት ስራ እየተሰራ መሆኑ ገልጸዋል።

የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን የክህሎት ማፍለቂያ ለማድረግ አበረታች ሥራዎች እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ውድድሩ በአሰልጣኝ፣ ሰልጣኝና ኢንተርፕራይዞች መካከል የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ልምድ የሚለዋወጡበትና የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት መሆኑንም አስረድተዋል።

ከሁሉ በላይ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ እንዲሆኑና የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን የገበያ ትስስር ችግር ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ኮሌጆች ያመረቱትን በራሳቸው በመሸጥ የውስጥ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም ኮሌጆቹ በፋንይናንስ አቅርቦት የሚያጋጥማቸውን እጥረት ለመፍታት እያስቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም