ለሰላም ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያላቸውን ተግባራት ለማስፋት እየተሰራ ነው - ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላም ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያላቸውን ተግባራት ለማስፋት እየተሰራ ነው - ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2017(ኢዜአ)፦ በተለያዩ ተቋማት እየተሰሩ ያሉ ለሰላም አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያላቸውን ተግባራት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።
የሰላም ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እያቀረበ ይገኛል።
በዚህ ወቅት የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ እንዳሉት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማጠናከርና ሀገራዊ ገዢ ትርክትን ለመገንባት በትምህርት ቤቶች የሰላም ክበባትን የማጠናከር ስራ ተሰርቷል።
በሀገር ግንባታና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ሊሂቃን ሊያበረክቱት በሚገባ ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ነው የተናገሩት።
ሀገራዊ ጥቅም፣ ማንነት፣ ዕሴትና ዘመኑን የዋጀ አርበኝነት ላይ ያተኮሩ አራት ሰነዶችን ማዳበር መቻሉንም ጠቅሰዋል።
እስከአሁን በ12 ዙር ከ80ሺህ በላይ የሰላም በጎ ፍቃድ ወጣቶችን ማሰማራት መቻሉን ገልጸው፤ በዚህም ወጣቶች ህብረ ብሄራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በተለያዩ ተቋማት እየተሰሩ ያሉ ለሰላም አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያላቸውን ተግባራት ሀገራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ተደጋጋሚ ግጭት የሚፈጠርባቸው አካባቢዎችን በመለየትና ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውንም አብራርትዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለሰላም ግንባታ አስተዋጽኦ ያላቸው 18 ሚሊየን የማህበረሰብ ክፍሎችን ማወያየት መቻሉንም ገልጸዋል።