በአፍሪካ የወጣቶችን ክህሎትና የፈጠራ አቅም ለማሳደግ የተግባር ትብብርና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2017(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ የወጣቶችን ክህሎትና ፈጠራ አቅም ለማሳደግ ከንግግር ያለፈ የተግባር ትብብርና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

"ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025" የአፍሪካ የትምህርት፣ አይ ሲ ቲ እና ክህሎት የሚኒስትሮች ስብሰባ "በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን ማስተማርና ማብቃት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።

የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካ ብሬይን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት አህጉራዊ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ይቆያል።


 

ጉባኤው የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ በሪፎርም፣ አቅም ግንባታ የቴክኖሎጂ ስትራቴጂካዊ ትብብር በመፍጠር የአፍሪካን የትምህርት ተደራሽነት ማስፋት ያለመ ነው።

በመርሀ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የትምህርት ሚኒስትር፣ ብርሀኑ ነጋ(ፕ/ር)፣ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የትምህርት ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሰው ልጅ መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ በማዘጋጀቷ ክብር ይሰማታል።

ጉባኤውም የትምህርት ጥራት፣ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ልህቀት አፍሪካን የሚያነቃቃ እና የወጣቱን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስን መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለአንድ ሀገር እድገት ትምህርት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ የመምህራንን ክብር መጠበቅ፣ ማነቃቃትና አቅማቸውን ማጎልበት፣ የተማሪዎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለትምህርት፣ ለክህሎት ማሳደግና ፈጠራ ቅድሚያ ትሰጣለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት፣ መሰረተ ልማት ለማስፋፋት፣ ፈጠራን ለማዳበር ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ ከኢትዮጵያ ራዕይ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ጠቅሰው፣ በጉባኤው ከንግግር ያለፈ ግልጽ እና ትርጉም ያለው ትብብር ገቢራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ዓለም የተለያዩ ችግሮች የሚስተዋሉባት በመሆኗ ከዚህ ችግር ለመውጣት በአፍሪካ ያለውን ተስፋ በትብብር መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

ትምህርት ቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ክብር ጭምር ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአፍሪካ ወጣቶች ትልልቅ ስራዎችን እያለሙ በመሆኑ ልጆቻችን ህልማቸውን እንዲያሳኩ በህብረትና በፍጥነት መስራት ይገባናል ብለዋል።

በአፍሪካ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶችን ለማሳደግ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ልንመራቸውና ልናነሳሳቸው ይገባል ነው ያሉት።


 

የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ(ፕ/ር)፣ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ጥንቃቄ እና አስተውሎት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካን የወደፊት እጣ ፋንታ ለመወሰን ወጣቶችን በክህሎት ማብቃትና በፈጠራ ማላቅ ይገባል ብለዋል።

በአፍሪካ በክህሎት፣ በቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ዘርፍ አዲስ ታሪክ ለመፃፍ በስፋት መነጋገርና መዘጋጀት አለብን ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም