የህብረቱ አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር የሀገራቱን ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው - ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካዔል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር ከውድድርነት ባለፈ የሀገራቱን ሰላምና ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካዔል ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተመሰረተበትን 116ኛ ዓመት በማስመልከት አምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር የመክፈቻ መርሃ ግብር በሻምበል አበበ ቢቂላ ስታዲየም ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካዔል በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባለፉት የለውጥ አመታት በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል፡፡

ሪፎርሙን ተከትሎ በሰው ሐብት ልማት፣ በቴክኖሎጂ፣ በሎጀስቲክስ፣ በምርመራ፣ በወንጀል መከላከልና በግንኙነት ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የሀገራችን አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡

ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካዔል በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ሩንዳ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳንና ጅቡቲ ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡


 

የውድድሩ ዋና አላማ የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር የምስራቅ አፍሪካን ሰላምና ደህንነት በትብብርና በቅንጅት ለማስከበር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወንድማማችነትን የማጠናከር፣ የእርስ በእርስ ልምድ ለመለዋወጥና ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት አላማ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

የ116ኛውን ብሔራዊ የፖሊስ በዓል አሁን ላይ በደረስንበትን ስኬት ሳንዘናጋ ለቀጣይ ተልዕኮ የምንዘጋጅበት ነው ብለዋል፡፡


 

በኬንያ ናይሮቢ የኢንተርፖል ቀጣናዊ ቢሮ ተወካይ ቦስኮ ጋሂጂ፥ በበኩላቸው፤ ዛሬ የተጀመረው ስፖርታዊ ውድድር ከስፖርት ጨዋታነት ባለፈ ቀጣናዊ ትስስርን በማጎልበት የተደራጁ ወንጀለኞችንና ሽብርተኝነትን ለመከላከል ጉልህ ድርሻ ያለው ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ የቀጣናውን ሀገራት ሁለንተናዊ ትስስር በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በጋራና በትብብር መስራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ስፖርታዊ ውድድር እስከ ሚያዚያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም