የምስራቅ አፍሪካን ስትራቴጂካዊ ቀጣናነት የሚመጥን ጠንካራ የፖሊስ ኃይል መገንባት ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካን ስትራቴጂካዊ ቀጣናነት የሚመጥን ጠንካራ የፖሊስ ኃይል መገንባት ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካን ስትራቴጂካዊ ቀጣናነት የሚመጥን ጠንካራ የፖሊስ ኃይል መገንባት ያስፈልጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተመሰረተበትን 116ኛ ዓመት በማስመልከት አምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር የመክፈቻ መርሃ ግብር በሻምበል አበበ ቢቂላ ስታዲየም ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን የሺህ ዘመናት የስልጣኔ መገለጫ፣ የነጻነታቸው ፋና ወጊ እንዲሁም የተቋማት ምስረታ ታሪካቸው ማስረጃ ናት ብለዋል።
ለዚህም ከ116 ዓመታት በፊት በ1901 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ፖሊስ ሁነኛ ምልክት መሆኑን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወቅቶች በዓለም አቀፍ መድረኮች ለአፍሪካውያን የተሟገተች ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር አህጉራዊና ቀጣናዊ የህብረት ድርጅቶችን መመስረቷን ተናግረዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች የጋራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ርዕይ ያለን ነን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ፖሊስም ከተለያዩ ሀገራት ጋር በወንድማማችነት መንፈስ በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የበርካታ ሀገራትን የፖሊስ ሠራዊት ማሰልጠኑን፣ አንዳንድ ሀገራት የፖሊስ ተቋም እንዲመሰርቱ ድጋፍ ማድረጉንም አውስተዋል።
የአፍሪካ ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግና ያለጠንካራ የፖሊስ ተቋማት አይታሰብም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በስልጠና የዳበረ፣ በቴክኖሎጂ የዘመነ፣ ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተናበበ መልኩ የሚጓዝ ብቁ የፖሊስ ኃይል መገንባት የግድ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ በእስያና በአፍሪካ አህጉራት መካከል ቁልፍ ቦታ ላይ የሚገኝ መሆኑን በመጥቀስ፤ ጠንካራ የፖሊስ ሠራዊት የሚያስፈልገው ቀጣና መሆኑን ተናግረዋል።
ሕጋዊ የሰዎች ዝውውር እና የሸቀጦች ግብይት ለማሳለጥ፣ ቀጣናዊ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ እየረቀቁ የመጡ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል፣ ዘመናዊ፣ ጠንካራና ዝግጁ የፖሊስ ኃይል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ህብረቶች በኩል በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅትን ጨምሮ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ አደረጃጀቱን እያስተካከለ፣ የአባላቱን የስልጠና ብቃት እያጠናከረ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ አቅሙን እያዳበረ ዓለም አቀፍ ልምዶችን እያካበተ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በጸጥታ ተቋማት የተካሄደው ሪፎርም ፖሊስን ይበልጥ ዘመናዊ፣ ዝግጁ፣ ደረጃውን የጠበቀ፣ ግዳጁን በብቃት የሚወጣ ተቋም እንዲሆን አድርጎታል ነው ያሉት።
አፍሪካን በሚመጥን መልኩ ተባብሮ መስራት እንደሚገባ በማንሳት፤ በየአካባቢው ያለንን እውቀት፣ ልምድ፣ ቴክኖሎጂና ብቃት ደምሮ በመጠቀም የተሻለ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ህልምን እውን ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅትም ፖሊሳዊ ህብረትና ወዳጅነትን እንደሚያጠናክር፣ ለአንድ ዓላማ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን እንደሚያዳብር አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ኢትዮጵያንና አፍሪካን በዓለም መድረክ ያስጠሩ ስመ ገናና ስፖርተኞችን ማፍራቱንም አውስተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር ቀጣናዊ ህብረትን ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።