ኢትዮጵያ በሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር ሁሉንም ሜዳሊያዎች አሸነፈች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር ሁሉንም ሜዳሊያዎች አሸነፈች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ በ5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ስፖርታዊ ውድድር ኢትዮጵያ በሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር ሁሉንም ሜዳሊያዎች አሸነፈች።
የኢትዮጵያ ፖሊስ የተመሰረተበትን 116ኛ ዓመት በዓል በማስመልከት 5ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር የመክፈቻ መርሃ ግብር ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተከናውኗል።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ የሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር እና የወንዶች የ400 ሜትር የዱላ ቅብብል የሩጫ ውድድር ተካሂዷል።
በሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ወርቅነሽ መሰለ፣ የኔነሽ ሺመክት እና ማተቤ ፍቃዱ በቅደም ተከተል ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት ሁሉንም ሜዳሊያዎች ወስደዋል።
በወንዶች የ400 ሜትር የዱላ ቅብብል ውድድር ደግሞ ኬንያ አንደኛ ኢትዮጵያ ሁለተኛ እንዲሁም ታንዛኒያ ሶስትኛ በመውጣት ውድድሩን አሸንፈዋል።
አሸናፊዎቹ አትሌቶች የሜዳሊያ ሽልማታቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እጅ ተቀብለዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት ሀገራት የሚሳተፉበት 5ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር እስከ ሚያዚያ 25/2017 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል።