የአፍሪካውያን ሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና ያለ ፖሊስ ተቋማት ጥንካሬ እና ብቃት የሚታሰብ አይደለም - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካውያን ሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና ያለ ፖሊስ ተቋማት ጥንካሬ እና ብቃት የሚታሰብ አይደለም - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካውያን ሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና ያለ ፖሊስ ተቋማት ጥንካሬ እና ብቃት የሚታሰብ አይደለም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ የኢትዮጵያ ፖሊስ የተመሰረተበትን 116ኛ ዓመት በዓልን በማስመልከት የሚካሄደውን 5ኛውን የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት የስፖርት ውድድር በውቧ አዲስ አበባ በይፋ አስጀምረናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘመናዊ የፖሊስ ተቋምን ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በመመስረት ግንባር ቀደምና ተምሳሌት ሀገር ናት ሲሉም ገልጸዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ያደረግነው የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም ደግሞ ፖሊስን ይበልጥ ዘመናዊ፣ ይበልጥ ዝግጁ፣ ይበልጥ ደረጃውን የጠበቀ፣ ይበልጥ ግዳጅ ፈጻሚ እያደረገው ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ኢትዮጵያንና አፍሪካን በዓለም መድረክ ያስጠሩ ስመ ጥር ስፖርተኞችን ያፈራ ተቋም ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አፍሪካዊ የሆኑ ስፖርታዊ ኩነቶችን እንዲያዘጋጅ ታሪኩም ልምዱም ይረዳዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አፍሪካውያን አፍሪካን በሚመጥን ደረጃ ተባብረን መሥራት አለብንም ብለዋል፡፡
በየአካባቢያችን ያለንን ዕውቀት፣ ልምድ፣ ቴክኖሎጂና ብቃት ደምረን ከተጠቀምን የተሻለ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ሕልማችንን እውን ማድረግ እንችላለን ነው ያሉት፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅትም ይሄንን ፖሊሳዊ ኅብረትና ወዳጅነት ያጠናክራል ሲሉም ተናግረዋል።
ለአንድ ዓላማ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ያዳብራል። ይህ የስፖርት ፌስቲቫል ኅብረታችን የበለጠ የሚጠናከርበት እንደሚሆን አምናለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመልዕክታቸው መልካም የውውድር ጊዜ እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።