በአማራ ክልል ከ269 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተሰማርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ269 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተሰማርተዋል
ወልዲያ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት 269 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የልማት ዘርፎች መሰማራታቸውን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
"ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሀሳብ የወልዲያ ከተማ ባለሃብቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና አጋር አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በወልዲያ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንዳሉት፣ የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማሳደግ በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህም በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 269 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺህ 899 አዳዲስ ባለሀብቶች በተለያዩ የልማት ዘርፎች መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
ከነዚህ መካከል 43ቱ በአምራች ኢንዱስትሪ፤ ዘጠኙ ደግሞ በአበባ ልማት የተሰማሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
እንደ አቶ እንድሪስ ገለጻ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 96ሺህ 81 ቶን የአበባ ምርት ወደ ውጪ ገበያ በመላክ 139 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማግኘት ተችሏል።
በሌላ በኩል 585 አምራች ኢንዱስትሪዎች 324ሺህ 409 ቶን ተኪ ምርቶችን በማምረት 40 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማዳን መቻላቸውን ነው ያስረዱት።
ዘርፉን ወደ ተሻለ እመርታ ለማሳደግና ለማጠናከር ሠላም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ የወልዲያ ከተማ ህዝብም ሰላሙን በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል።
የሰላሙ ሁኔታ እንዲጠናከር መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ይበልጥ ለማስፋፋትም ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።
ሰርቶ ለማትረፍና ለመጠቀም ሰላም አስፈላጊ በመሆኑ መንግስት ለዘላቂ ሰላም ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ህብረተሰቡም ሳያውቁ ወደ ጥፋት የገቡ ልጆቹን መክሮ እንዲመልስ አስገንዝበዋል።
የወልዲያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው በከተማው አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
አዳዲስ ባለሃብቶች እንዲመጡ፣ በብድር አገልግሎት ላይ ያለውን ችግር ለመፍታትና መሬትን ከሦስተኛ ወገን ነጻ በማድረግ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ቁርጠኛ ነው ሲሉም አረጋግጠዋል።
ተሳታፊ ባለሀብቶች በበኩላቸው የተሟላ የውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፣ በብድር አገልግሎት ላይ የሚታየውን መጉላላት መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
በወልዲያ ከተማ አስተዳደር በአራት ቢሊዮን ብር ካፒታል የግንባታ ፈቃድ ያወጡ ሰላሳ ሰባት ባለሃብቶች እንዳሉና አስራ አንዱ ወደ ምርት መግባታቸውን የተገኘው መረጃ ያሳያል።