ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የያዘችውን የልማት ዕቅድ በውጤታማነት ለማሳካት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የያዘችውን የልማት ዕቅድ በውጤታማነት ለመተግበር እና ዘላቂ ዕድገት ለማስመዝገብ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።

በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የሚመራውና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችን ያካተተው የኢትዮጵያ ልዑክ በቅርቡ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆን ከተሾሙት ኒጌል ክላርክ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርጓል።

ውይይቱ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው እኤአ የ2025 የዓለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የጸደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ነው።

በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ውጤታማነትና ድርጅቱ በቅርቡ በኢትዮጵያ በነበረው የፕሮግራም ግምገማ በቀረቡ ግኝቶች ላይ ያተኮረ ውይይት ማድረጋቸውም ተጠቁሟል።

ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳን በመተግበር ኢኮኖሚውን ለማዘመን፣ ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ፣ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማበረታታትና የስራ ዕድል ለመፍጠር በምታደርገው ጥረት ለሚያደርገው የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ አመስግነዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኒጌል ክላርክ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በመተግበር ግሽበትን ለማውረድ፣ ወደ ውጭ የሚላክ ምርትን ለማሳደግ፣ ገቢ ለማሳደግ እና ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የያዘችውን የልማት ዕቅድ በውጤታማነት ለመተግበርና ዕድገትን ለማሳካት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም