የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የስፖርት ትጥቅ አልባሳትን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እያስቻለ ነው - ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የስፖርት ትጥቅ አልባሳትን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እያስቻለ እንደሚገኝ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትብብር የተዘጋጀው የ2017 ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በውድድሩ ማስጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ታምርት የጎዳና ላይ ውድድር የኢትዮጵያን ምርት ለዓለም የማስተዋወቅ ዓላማ ያነገበ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ በሚደምቅበት የአትሌቲክስ የስፖርት ዘርፍ ውድድር መካሄዱም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማስተዋወቅ ገንቢ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ላደረገው የሩጫ ውድድር መካሄድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ተወዳዳሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።


 

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫም አምባሳደሮች የተሳተፉበት እና ለአሸናፊዎች ላቅ ያለ ሽልማት መዘጋጀቱ ከወትሮው ለየት እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ በስፋት እያቀረበች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡

አምራችና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ስፖርታዊ ውድድር ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የስፖርት ትጥቅ አልባሳትን በሀገር ውስጥ መተካት እያስቻለ ነው ብለዋል።

የስፖርት ትጥቅ አምራች ኢንዱስትሪ ትስስርን በማሳደግ የስፖርት ትጥቆች በስፋት እንዲመረቱና ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲቀርቡ የማድረግ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ምርት በመጠቀም ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ማዘውተር እንደሚኖርባቸውም አስታውቀዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው ባለፉት የለውጥ ዓመታት በስፖርት ልማት ላይ የተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት ልማትን በማስፋት ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ባህሉ ያደረገ ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የስፖርት ትጥቅን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በ2017 ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተሳታፊዎች መካከል ኃይለ-ሚካዔል ማስረሻ፣ መቅደስ ጸጋዬ እና አዲስ በቀለ ይገኙበታል።


 

ወጣት ኃይለ-ሚካዔል ማስረሻ በሰጠው አስተያየት መርሐ ግብሩ ከስፖርታዊ ውድድርነት ባሻገር የሀገር ውስጥ ምርትን እንድንጠቀም ግንዛቤ የሚፈጥር ነው ብሏል፡፡

ሌላኛዋ ተሳታፊ መቅደስ ጸጋዬ በበኩሏ የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሚትር ሩጫ ኢትዮጵያውያን ይበልጥ እንዲተባበሩ እና ለጋራ ግብ እንድንተጋ የሚያበረታታ ነው ብላለች።


 

በውድድሩ የሀገርን ምርት ለማስተዋወቅና ሁሉም እንዲጠቀመው ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ የሩጫው ተሳታፊ አዲስ በቀለ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በወንዶች ሞገስ ጥዑማይ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ፣ ጅራታ ሌሊሳ በግል እና ሲዳ አማና ከሸገር ከተማ በቅደም ተከትል የወርቅ፣ የብር እና የነሀሰ ሜዳሊያ በማግኘት የ300ሺህ፣ የ200ሺህ እና የ100ሺህ ብር ሽልማት ተረክበዋል።

በተመሳሳይ በሴቶች የሩጫ ውድድር ገመኔ ማሚቴ ከኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ፣ አበዙ ከበደ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ማርታ አለማየሁ በግል በቅደም ተከትል የወርቅ፣ የብር እና የነሀሰ ሜዳሊያ በማግኘት የ300ሺህ፣ የ200ሺህ እና የ100ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም