የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በዘጠኝ ወራት በ12 ሺህ 540 ቱሪስቶች ተጎብኝቷል

ወልቂጤ፤ ሚያዚያ 19/2017(ኢዜአ)፡-የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክን በዘጠኝ ወራት 12 ሺህ 540 ቱሪስቶች እንደጎበኙት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል  ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤትአስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ መስፍን ተካ እንደገለጹት ፓርኩ የተለያዩ ብርቅዬ እንስሳትና እጽዋት መገኛ እንዲሁም ውብ የተፈጥሮ ገጽታ ያለው ነው።


 

በፓርኩ ስድስት ብርቅዬ አዕዋፍ፣ የእጣን ዛፍና ለመድሃኒትነት የሚውሉ ተክሎች መገኛና በቀን እስከ 500 ጎብኚዎችን የሚያስጠቅሙ ፍልውሃ እና ማራኪ ሥፍራዎች አካቶ የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርኩን ለማስተዋወቅ በተሰራው ሥራ  የጎብኚ ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን ጠቅሰው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 12 ሺህ 540  ቱሪስቶች ፓርኩን ጎብኝተዋል ብለዋል።

ከእነዚህ ውስጥም 40ዎቹ  የውጭ ሀገር ቱሪስቶች መሆናቸውን ነው የገለጹት።


 

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ ፓርኩን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ8 ሚሊዮን 100 ሺህ ብር በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን ይህን ገቢ አጠናክሮ ለማስቀጠልም በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ለፓርኩ በተሰጠው ትኩረት  ህገ ወጥ የመሬት ወረራና የደን ጭፍጨፋን ለማስቆም መቻሉንም ተናግረዋል።

በፓርኩ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የማህበረሰብ ሎጅ ለመገንባት የዲዛይን ሥራ ተጠናቆ ወደ ተግባር ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አንስተዋል።

ከክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ጋር በመሆን 3 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ለመገንባት ውል መገባቱንም ሀላፊው አቶ መስፍን ጠቁመዋል።


 

የፓርኩ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ብርሃኑ መብራቱ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ በፓርኩ የተለያዩ የዱር እንስሳት፣ የተፈጥሮ ደኖችና አዕዋፋት፣50 የሚደርሱ ፍል ውሃዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ የሉቄ እና የጃቱ ፍል ውሃዎች ፓርኩ የተለየ ገጽታ እንዲኖረው ካደረጉት መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል።  

በፓርኩ ተፈጥሯዊ መስህቦችን የማልማት፣ የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ ጎን ለጎን ይከናወናል ብለዋል።


 

የፓርኩ ስካውት አቶ አራጋው ካሳ ለደኑ በመንግስት ተገቢ ትኩረት በመስጠት ጥበቃ መደረጉ ብዝሃ ህይወትን ጠብቆ ለማቆየት እያስቻለ መሆኑን ገልፀው ህገወጥ ሰፈራና የደን ጭፍጨፋን መግታት መቻሉ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወንና ብዝሀ ህይወትን ለመጠበቅ ማገዙንም ነው የተናገሩት።

ፖርኩን ሲጎበኙ ከነበሩት መካከል ወጣት ሶሌ ጀቢሳ በፓርኩ የተለያዩ የተፈጥሮ ገጽታ ያላቸው መስህቦችን መመልከቱን ተናግሯል።

በፓርኩ የቱሪስቶች ማረፊያና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በማዘጋጀት የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜን ለማራዘም መስራት እንደሚገባም ነው የገለጸው። 


 

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ጎብኚ ቤተልሔም ኩሶ ውብ፣ ሳቢና ማራኪ የተፈጥሮ ሀብቶች በፓርኩ ውስጥ እንዳሉ መመልከቷን ገልጻለች።

በፓርኩ ቆይታ ያገኘችው የመንፈስ እርካታ በቀጣይም ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ፓርኩን ለመጎብኘት እንዳነሳሳት ገልጻለች። 

ከፓርክ አካባቢ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ፍቅሬ በሰኔ ፓርኩ በብዝሃ ህይወት የታደለ በመሆኑ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ለማስጠበቅ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በውስጡ ያሉ እንስሳትና እጽዋትን ጨምሮ ለፓርኩ ብዝሀ ሕይወት መጠበቅ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በማገዝ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን የሚገኘው ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ጠቅላላ የቆዳ ስፋት 360 ኪሎ ሜትር ስኩዌር መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም