ተጠባቂው የለንደን ማራቶን - ኢዜአ አማርኛ
ተጠባቂው የለንደን ማራቶን

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 19/2017 (ኢዜአ)፡- 45ኛው የለንደን ማራቶን ዛሬ ረፋድ ላይ ይካሄዳል።
በሁለቱም ጾታዎች የሚደረጉ የዓለም የአትሌቲክስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።
በሴቶች አትሌት ትዕግስት አሰፋ እና አትሌት ሲፋን ሀሰን የሚያደርጉት ፉክክር በጉጉት እንደሚጠበቅ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል።
ሁለቱ አትሌቶች በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በማራቶን ውድድር እስከ መጨረሻው እልህ አስጨራስ ፉክክር አድርገው ሲፋን አንደኛ፣ ትዕግስት ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ነው።
አትሌቶቹ ከኦሊምፒኩ መልስ ዳግም በወሳኝ የአትሌቲክስ መድረግ ላይ ተገናኝተዋል።
አትሌት ትዕግስት 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ በርቀቱ የዓለም ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት ባለቤት ናት።
ሲፋን 2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ የዓለም ሶስተኛ ፈጣን ሰዓትን አስመዝግባለች።
ኬንያዊቷ የማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ሩት ቼፕጌቲች እና የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ የሆነችው ሌላኛዋ ኬንያዊ አትሌት ፔሬዝ ቼፕቺርቺር በውድድሩ ላይ አይሳተፉም።
ሌላኛዋ ኬንያዊ ጆይስሊን ጄፕኮስጌ የሀገሬው ሰዎች ተስፋ የጣሉበት አትሌት ናት።
በወንዶች በፓሪስ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው አትሌት ታምራት ቶላ እንዲሁም ኬንያዊው ኢሊውድ ኪፕቾጌ እና ሌላኛው የሀገሩ ልጅ አሌክሳንዳር ሙቲሶ ሙናዮ የማሸነፉን የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል።
ሙናዮ የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ነው።
ዩጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ ሌላኛው ተጠባቂ አትሌት ነው።
አንጋፋው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በጉዳት ምክንያት ከውድድሩ ውጪ መሆኑ የሚታወስ ነው።
በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸንፉ አትሌቶች በተመሳሳይ የ55 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ያገኛሉ።
እ.አ.አ በ1981 የተጀመረው የለንደን ማራቶን በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የጎዳና ላይ ውድድር ሲሆን በዓለም ላይ ተጠባቂ ከሆኑ ውድድሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ነው።