ቀጥታ፡

የአማራ ክልልን የማተራመስ እቅዱ የከሸፈበት ጽንፈኛ ቡድን አሁን ላይ ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ተጠምዷል - ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2017(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልልን የማተራመስ እቅዱ የከሸፈበት ጽንፈኛ ቡድን አሁን ላይ ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ተጠምዷል ሲሉ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ተናገሩ።

የአማራ ክልል የጸጥታ ተቋማትን መልሶ በማደራጃትና በማጠናከር ረገድ ውጤታማ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በአማራ ክልል ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በመፈጸም የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር ማሳየቱን አስታውሰዋል።

መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የጽንፈኛ ቡድኑን የጥፋት ተግባር በመቀልበስ ረገድ ውጤታማ ስራ ማከናወኑንም አንስተዋል።

በክልሉ እየተወሰደ ካለው ህግ የማስከበር እርምጃ በተጓዳኝ ጽንፈኛ ቡድኑ የጥፋት መንገዱን እንዲተው በመንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ መቅረቡን ጠቅሰዋል።

በዚህም በርካታ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በተገኘው ሰላም ህብረተሰቡ ሲያነሳቸው ለቆዩ የልማትና የሰላም ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ የመስጠት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ጽንፈኛ ቡድኑ ክልሉን የማተራመስ እቅዱ አልሳካለት ሲል መንግስት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳደረሰ በማስመሰል የሀሰት መረጃ እያሰራጨ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁን ያለው መንግስት በህዝብ የተመረጠና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው መሆኑን አንስተው፤ ሰላማዊ ዜጎችን የመጠበቅና በልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራን በትኩረት እያከናወነ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የጸጥታ ኃይሉም የህይወት መስዋትነት በመክፈል ጭምር የክልሉ ነዋሪዎች ሰላም እንዲያገኙ አይተኬ ሚና ትወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል ብለዋል።

በተቃራኒው ጽንፈኛ ቡድኑ በክልሉ አረጋዊያንን፤ የሀገር ሽማግሌዎችና መምህራንን በማንገላታትና በመግደል ጭምር ሰላማዊ ዜጎች ላይ ግፍና ሰቆቃ መፈጸሙን ነው ያብራሩት።

በክልሉ ቀጣይነት ባለው መልኩ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንም ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ የጸጥታ ኃይሉን መልሶ የማደራጀትና የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

መልሶ የማደራጀት ስራው በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ካለው የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም ስራ ጋር የሚጣጣምና የተናበበ መሆኑንም እንዲሁ።

እስከ አሁን ባለው ሂደትም የክልሉን ጸጥታ ኃይል መልሶ በማደረጃት እየተከናወነ ያለው ሪፎርም ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የአፈር ማዳበሪያ ተደራሽ እንዲሆን የጸጥታ ሃይሉ ቀን ከሌት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉ ነዋሪዎች ከመንግስት ጎን በመሆን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስፈን የሚከናወነውን ስራ በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ መሆኑንም ነው ኮሚሽነር ዘላለም የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም