ቀጥታ፡

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለኢትዮጵያ ፖሊስ ስፖርተኞች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አስረከቡ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በአምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ድርጅት የስፖርት ውድድር ላይ ለሚሳተፉ የኢትዮጵያ ፖሊስ ስፖርተኞች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አስረክበዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት መንደር በመገኘት ባደረጉት ንግግር የወከላችሁት ብዙ መሥዋዕትነት የተከፈለበት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ነው ብለዋል።

ስለሆነም በስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ በመሆን የወከላችሁትን መላ የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት ክብር ከፍ በማድረግ በድል አድራጊነት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እንድታውለበልቡ በማለት ስፖርተኞቹን ማሳሰባቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት የስፖርት ውድድር ከነገ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።

ውድድሩ የተዘጋጀው 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታ በዓል ቀንን በማስመልከት ነው።

በስፖርት ውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የጂቡቲ፣ የኬንያ፣ የታንዛኒያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የዩጋንዳ እና የሩዋንዳ የፖሊስ ተቋማት በስድስት የስፖርት አይነቶች ይሳተፋሉ።

አትሌቲክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ዒላማ ተኩስ፣ ቦክስ፣ ዳርት እና እጅ ኳስ ውድድሩ የሚካሄድባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም