ከሰኔ 2017 ጀምሮ ፓስፖርት ለመውሰድ የፋይዳ መረጃ ይዞ መቅረብ ይጠበቃል

አርባምንጭ፤ሚያዝያ 18/2017 (ኢዜአ)፦ከሰኔ 1፣ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ፓስፖርት በመጠባበቅ ላይ ያሉ ግለሰቦች ፓስፖርት ለመውሰድ ሲመጡ የፋይዳ መረጃቸውን ይዘው መቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

የፋይዳ መታወቂያ ለፓስፖርት አገልግሎት ቅድመ ሁኔታ መስፈርት እንዲሆን የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት በአርባምንጭ ከተማ ተፈርሟል።

በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና በዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራም መካከል የተፈረመው ስምምነትም ከሰኔ 1 2017 ዓ.ም ጀምሮ የፋይዳ መታወቂያን ለፓስፖርት አገልግሎት ከሚያስፈልጉ ዋና ሰነዶች ውስጥ በማካተት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፥ ተቋሙ የጀመራቸውን የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር ከሰኔ 01/2017 ዓ/ም ጀምሮ የፋይዳ መታወቂያን ለፓስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ቅድመ ሁኔታ ለማድረግ የዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

የፋይዳ ድጅታል መታወቂያ የድጅታል ትራንስፎርሜሽን አስቻይ ከመሆኑም ባሻገር ዘመናዊ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርያስላሴ በበኩላቸው፥ ስምምነቱ ማንነትን በማጭበርበር የተለያዩ ሰነዶችን ለማግኘት የሚደረግን ጥረት የሚገታ ነው ብለዋል።

አክለውም ለዜጎች አገልግሎት ቅልጥፍና ፣የሥራ ድግግሞሽንና የሀብት ብክነትን የሚያስቀር ነው ብለዋል።

ዜጎች የፓስፖርት አገልግሎት ጥያቄ አቅርበው ፓስፖርት ለመውሰድ ሲመጡ የፋይዳ መታወቂያቸውን በወረቀት ወይም በስልካቸው ይዘው በመምጣት አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ አስገንዝበዋልል።

ተገልጋዮች የፋይዳ ልዩ ቁጥራቸውን በመያዝ፣ QR ኮዱን በወረቀት አትመው፣ዲጂታል ኮፒውን በ"Fayda ID” application በኩል ይዘው ወይም ትክክለኛውን QR የያዘ ሌላ አማራጭ ተጠቅመው ይዘው በመምጣት ብቻ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ነው የተባለው።

አገልግሎቶች ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር መተሳሰራቸው አንድ ወጥ ደረጃ ያለው እና የተናበበ መረጃ በብሔራዊ ደረጃ እንዲኖር በማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም