ለከተማችን ሰላምና የልማት እቅዶች መሳካት የድርሻችንን ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ ነን- የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

ደሴ፤ሚያዚያ 18/2017( ኢዜአ)፡-ለከተማችን ሰላምና የልማት እቅዶች መሳካት የድርሻችንን ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ ነን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የደሴ ከተማ የኮሪደርና ሌሎች ልማቶች ውጤታማ የሆኑት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የልማቱም ይሁን የሰላም አጋር መሆኑን በተግባር በማሳየቱ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሸህ ሙስጠፋ አህመድ፤ የሁሉም ነገር መሰረት ሰላም በመሆኑ ሰላምን አስቀድመን የልማት ስራዎችን አስከትለን በቅንጅት በመስራታችን ተጠቃሚዎች ሆነናል ብለዋል።

በደሴ ከተማ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን ኮንፈረንስን ጨምሮ የጎብኝዎች እንቅስቃሴ በመኖሩ ከቱሪዝም ዘርፉ ገቢ እያገኘን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በቀጣይም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እና የአስተዳደር መዋቅር ጋር በመተባበር ለዘላቂ ሰላምና ልማታችን ዘብ እንቆማለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ቀሲስ ዘላለም ቢሆነኝ፤ የእምነት ተቋማትና የኃይማኖት አባቶች የመጀመሪያ ተግባር ሰላምን መስበክና ስለ ሰላም አብዝቶ መጸለይ በመሆኑ በዚሁ መልኩ እያገዝን ነው ብለዋል።

ሌላኛዋ የደሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እቴነሽ አባተ፤ የደሴ ከተማ የሰላምና አብሮነት እሴቶች ለሌሎችም ጥሩ ማሳያ የሚሆን ነው ብለዋል።

ለከተማችን ሰላምና የልማት እቅዶች መሳካት የድርሻችንን ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ ነን በማለት ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ደህንነት መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ፤ የደሴ ከተማ አስተማማኝ ሰላም መሰረቶች የህዝቡና የጸጥታ ሃይሉ ጥብቅ ትስስርና መተጋገዝ ያመጣው መሆኑን ገልጸዋል።

በየሰፈሩ ነዋሪው ተደራጅቶ ሰላሙን እያስጠበቀና እየተከታተለ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ደሴ ከተማ የትኛውም አካባቢ ወንጀል ፈፃሚዎች በቅጽበት የሚያዙ መሆኑን ጠቅሰው፥ በሁሉም አካባቢ አስተማማኝ ሰላም መኖሩን አረጋግጠዋል።

በከተማው በየእለቱ የተለያዩ ሁነቶችና በርካታ ኮንፈረንሶች የሚካሄዱ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም የከተማው ነዋሪ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የሆቴሎች፣የምግብና መዝናኛ ቤቶች እንዲሁም በሌሎች የአገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩት ሰዎች በእጅጉ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።

በመሆኑም የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የወጣቱ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አጠቃላይ የነዋሪዎች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም