ቀጥታ፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ9 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ቱሪስቶች መዲናዋን ጎብኝተዋል-ቢሮው

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፡-በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ9 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች መዲናዋን መጎብኝታቸውን የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ሁንዴ ከበደ ለኢዜአ እንዳሉት፥ ከተማዋን የሚጎበኙ ጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ይህ የውጭ እና የአገር ውስጥ ጎብኝዎች ቁጥር ከባለፈው አመት ዘጠኝ ወራት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 9 ሚሊየን 740 ሺህ በላይ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ቱሪስቶች መዲናዋን መጎብኝታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በከተማዋ የተካሄዱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ፌስቲቫሎች ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ማደግ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልፀዋል።

እንዲሁም በከተማዋ የተሰሩ የቱሪስት መዳረሻ ልማትና የኮሪደር ልማቱ ለቱሪዝም ዘርፉ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም ጨምረው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ኤንዲ አሰፋ በበኩላቸው፥ ከቅርብ አመታት ወዲህ እየተሰሩ ያሉ የቱሪዝም ልማት ስራዎች ወደ አገሪቱ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተማዋን ከአለም ከተሞች ጋር በቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪ እያደረጋት መሆኑንም ተናግረዋል።

ከመዳረሻ ልማት ባሻገር ከተማዋ ለስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም፣ ኮንፍረንስ ቱሪዝም ተመራጭ መሆኗም ለከተማዋ ቱሪዝም እድገት አስተዋፅኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም