በኢፌዴሪ አየር ኃይል የሶስተኛ አየር ምድብ ለአረጋዊያን ማዕድ አጋራ - ኢዜአ አማርኛ
በኢፌዴሪ አየር ኃይል የሶስተኛ አየር ምድብ ለአረጋዊያን ማዕድ አጋራ
ድሬደዋ፤ሚያዝያ 18/2017(ኢዜአ) ፡- በኢፌዴሪ አየር ኃይል የሶስተኛ አየር ምድብ በድሬደዋ አሰገደች አሰፋ የአረጋዊያን መጦሪያ ማዕከል ለሚገኙ አረጋዊያን ዛሬ ማዕድ አጋራ።
መረሃ ግብሩ የተከናወነው የሶስተኛ አየር ኃይል ምድብ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደረጀ ቡሽሬ፣ምክትል አዛዥ ለአየር ሎጀስቲክስ ሌተናል ኮሎኔል ቴዎድሮስ ካሳሁን እና ሌሎችም የሰራዊቱ አባላት በተገኙበት ነው።
ሌተናል ኮሎኔል ቴዎድሮስ ካሳሁን በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ሰራዊቱ የአገር ሉአላዊነትን በአስተማማኝ መንገድ ከመጠበቁ በተጓዳኝ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው መረሃ ግብርም በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከሰራዊት አባላትና ሲቪል ሰራተኞቹ ባዋጡት ከ3 መቶ ሺህ በላይ ለአረጋውያን ማዕድ ማጋራታቸውን ተናግረዋል።
ማዕድ የማጋራት መረሃ ግብሩን ያዘጋጁት በተለያዩ ዘርፍ ለሀገራቸው አስተዋጽኦ ያበረከቱ እናት አባት አረጋውያንን በመጎብኘት ከጎናቸው መሆናችንን ለማሳየት እንደሆነ አስረድተዋል።
ለአረጋውያኑ ከተጋራው መካከል የምግብ ዘይት፣ ዱቄትና ሩዝ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
የአሰገደች አሰፋ አረጋውያን መረጃ ማዕከል ባለፉት ዓመታትም ሰራዊቱ ካለው ላይ በማዋጣት ድጋፎች ሲያደርግ እንደቆየም አስታውሰዋል።
የማዕከሉ ተወካይ ወይዘሮ እመቤት መኮንን ፤የሶስተኛው አየር ምድብ ለማዕከሉ አረጋዊያን ተደጋጋሚ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን ማሳየቱን በማውሳት ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።