ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ የዓለምን ህዝብ በቅንነት እና በጎነት አገልግለዋል-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ የዓለምን ህዝብ በቅንነት እና በጎነት አገልግለዋል-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፦ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ ለተገፉ ድምጽ፣ ቀን ለጎደለባቸው መከታ በመሆን የዓለምን ህዝብ በቅንነት እና በጎነት አገልግለዋል ሲሉ የኤፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ የመሥዋዕተ ቅዳሴ፣ ሥርዓተ ፍትሐት እና የሐዘን መግለጫ ፊርማ የማኖር ሥነ-ሥርዓት በልደታ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል ተካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ የኤፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴን ጨምሮ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዲሁም የተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ታድመዋል።
የኤፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በዚሁ ወቅት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ ለተገፉ ጠበቃ ችግር ለጎበኛቸው ሁሉ ድምጽ በመሆን የዓለምን ህዝብ በቅንነት እና በጎነት ማገልገላቸውን ገልጸዋል።
እንዲሁም ሰላም ባጡ አገራት ሁሉ ፈጥነው የሚደርሱ ታላቅ አባት እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ ቀን ለጎደለባቸው በጸሎት በማስታወስ ትልቅ አገልግሎት መስጠታቸውን ገልጸው፤ ዓለም ትልቅ ሰው ማጣቷን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ አቡነ ተስፋ ስላሴ በበኩላቸው፤ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ ለፈጣሪያቸው ያደሩ እንደነበሩ ተናግረዋል።
የተቸገሩን የሚያግዙ ያዘኑን የሚያጽናኑ አባት እንዲሁም ለዓለም ሰላም የጸለዩ ፤የሰሩ ትሁት እና ሩህሩህ አባት እንደነበሩ አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ ችግረኞችን ማገዝ ስለ ሰላም መጸለይን ከእርሳቸው ታሪክ መማር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ከተገኙ የእምነቱ ተከታዮች መካከል ሙሉነህ ተስፋዬ፤ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ የሰው ልጅ ሁሉ ያለምንም ልዩነት በፍቅር ያስተማሩ አባት እንደነበሩ ተናግሯል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ የምስራች አሰፋም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ ከተቸገሩና ካዘኑ ጋር አብረው የሚያዝኑ አባት እንደነበሩ ገልጻለች።
በተለይም ወጣቶች ትርጉም ያለው ህይወት እንዲኖራቸው የመከሩ የሰሩ አባት እንደነበሩም ተናግራለች።