የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በተያዘው ዓመት በታቀደው መሰረት ያድጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በተያዘው ዓመት በታቀደው መሰረት ያድጋል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በተያዘው ዓመት በታቀደው መሰረት በስምንት ነጥብ አራት በመቶ እንደሚያድግ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስታወቀ።
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሚያዚያ 17 እስከ 18 ቀን 2017 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን ካካሄደ በኋላ መግለጫ አውጥቷል።
ለሁለት ቀናት ሲካሔድ የቆየው የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቀቀ
በመግለጫውም የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች በዝርዝር መመልከቱን ገልጿል።
ኢትዮጵያ በ2018 ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን ለመሻገር፤ በ2023 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን፤ በ2040 ደግሞ ዓለም አቀፍ የብልጽግና አርአያ ለመሆን ያስቀመጠችው ርዕይ እንደሚሳካ የሚያረጋግጡ የስኬት ፍንጮች መታየታቸውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡
የስኬት ፍንጮች ፓርቲው የያዘው ፍኖተ ብልጽግና ትክክል መሆኑን እንደሚያመለክትም አትቷል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ እስከ አሁን ያለው አፈፃፀም የሚያሳየው በያዝነው ዓመት አጠቃላይ ኢኮኖሚው በታቀደው መሠረት በስምንት ነጥብ አራት በመቶ የሚያድግ መሆኑን የሥራ አስፈጻሚው መገምገሙን አረጋግጧል።
በዘርፍ ደረጃ ግብርና በስድስት ነጥብ አንድ በመቶ፣ ኢንዱስትሪ በ12 ነጥብ 8 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ በ12 በመቶ፣ ኮንስትራክሽን በ12 ነጥብ 3 በመቶ፣ አገልግሎት ደግሞ በሰባት ነጥብ አንድ በመቶ የሚያድጉ መሆናቸው መገምገሙን አመልክቷል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጠቅላላ የመንግሥት ገቢ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ134 በመቶ ብልጫ ማሳየቱንም አመልክቷል።
የውጭ ብድር ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ መውረዱን የጠቆመው መግለጫው፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡት ስድስት ዋና ዋና ምርቶች፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸሩ ከ82 በመቶ እስከ 386 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን አመልክቷል።
በስንዴ፣ በሩዝ፣ በቡና፣ በሻሂ ቅጠል እና በፍራፍሬ ምርቶች በአፍሪካ ቀዳሚ ሆኖ ለመውጣት እየተደረገ ያለው ትግል ፍሬ እያፈራ መሆኑን እንደሚያሳይ መግለጫው አረጋግጧል።