ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት ናት - ሌተናል ጄነራል መሐመድ ባሬድ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት ናት ሲሉ የሞሮኮ ሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄነራል መሐመድ ባሬድ ገለጹ።

ለአፍሪካ ሰላም እና ደህንነት እያደረገች ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።

የሞሮኮ ወታደራዊ ልዑካን ቡድን ከመከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ፋይናንስ ስራ አመራር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ ጋር ውይይት አድርጓል።

የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድን በመወከል ውይይቱን የመሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢትዮጵያ የጋራ ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት እና የማይቀለበስ ጠንካራ ወታደራዊ ግንኙነት ለመመስረት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ትብብሩን በመከባበር እና በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የሞሮኮ ሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄነራል መሐመድ ባሬድ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት ናት ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓትም ለአህጉሪቷ ሰላም እና ደህንነት እያበረከተች ላለው ወታደራዊ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የሀገራቱ ወታደራዊ ትብብርም ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነም አመልክተዋል።

በአጠቃላይ የሞሮኮ ልዑካን ቡድን ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ሰራዊት ያላቸው አክብሮት ታላቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በውይይቱ ዋነኛ ወታደራዊ፣ሀገራዊ እና አህጉራዊ ትኩረት ናቸው ተብለው በተለዩ የሰላም እና አጠቃላይ ወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን የሁለቱም ሀገራት አመራሮች ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይም የመከላከያ ውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ተሾመ ገመቹን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም