በሐረሪ ክልል 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ የምስረታ በዓልን አስመልክቶ የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ የምስረታ በዓልን አስመልክቶ የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል የሚገኙ የጸጥታ ተቋማት 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ የምስረታ በዓልን አስመልክቶ በከተማው የጽዳት ዘመቻ እና አረንጓዴ ስፍራዎችን እንክብካቤ ዛሬ አካሂደዋል።
የጽዳት ዘመቻው በከተማው፣ በጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ እና ዙሪያ የተደረገ ሲሆን በዘመቻው መንገዶችን ከመጥረግ ጀምሮ የአረንጓዴ ስፍራዎችን የመንከባከብ ስራ ተከናውኗል።
በጽዳት ዘመቻው ላይ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ረምዚ ሱልጣን ጨምሮ የክልሉ ፖሊስ እና የፌደራል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት ተገኝተዋል።
ኮሚሽነር ረምዚ ሱልጣን እንደገለፁት ሐረር ከተማን ስሟን እና ክብሯን የሚመጥን ጽዳት እንዲኖራትና ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ለቱሪዝም ሳቢ ከተማ እንድትሆን የክልሉ መንግሥት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ ነው።
ህብረተሰቡም ጽዱና አረንጓዴ ሐረርን በመፍጠር ሂደት ከመንግሥት ጎን በመሆን የአካባቢውን ጽዳት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሚሽነሩ በጽዳት ዘመቻው ላይ ለተሳተፉ የጸጥታ ተቋማት አመራሮችና አባላት ምስጋና ማቅረባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።