ቀጥታ፡

አካዳሚውና የጋራ ምክር ቤቱ በአቅም ግንባታና ምርምሮች በጋራ ለመሥራት የደረሱበትን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአቅም ግንባታ፣ ጥናትና ምርምሮች ላይ በጋራ ለመሥራት የደረሱበትን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ  ጀመሩ።       

ተቋማቱ ህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

የመግባቢያ ሰነዱን ወደ መሬት ለማውረድ ከሁለቱ ተቋማት የተውጣጣ የቴክኒክ ቡድን በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ የጋራ ዕቅድ አዘጋጅቷል።     

በዛሬው ዕለትም በተዘጋጀው ዕቅድ ዙሪያ የአካዳሚው እና የጋራ ምክር ቤቱ አመራር አባላት የተወያዩ ሲሆን፤ በአቅም ግንባታ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች በጋራ የመስራት እንቅስቃሴ ጀምረዋል።


 

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰረት ደስታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በስምምነቱ መሰረት አካዳሚው ለፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባለት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ይሰጣል።  

በዚህም ያሉ ክፍተቶችን በጥናት በመለየት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የፖሊሲ ማማከር ሥራዎችንም አካዳሚው እንደሚያከናውን አብራርተዋል።      

በዚህ ዓመት ለ120 የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንደሚሰጥ ገልጸው፤ ሥልጠናው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።   

በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ሁኔታዎችን በላቀ ደረጃ የሚረዳና በቂ ግንዛቤ የጨበጠ አመራር ወሳኝ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቷ፤ በተቋማቱ መካከል የተደረገው ትብብር ይሄን ግብ ለማሳካት ያለመ ነው ብለዋል።  


 

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፤ ያለን አንድ አገር ነው፤ ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት መረባረብ አለብን ብለዋል።  

በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት የሚያስችሉ ሀሳቦች የሚንሸራሸርባቸው የውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱም ጠቁመዋል።   

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍኖ የቆየውን የፖለቲካ ስብራት ለመጠገን መሰል ትብብሮች ቁልፍ ሚና እንዳላቸውም ነው ያስረዱት።  

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ ምክር ቤቱ ከአካዳሚው ጋር በፈጠረው ግንኙነት አገራዊ አስተዋጽኦን የሚያሳድግበት ልምድ የቀሰመ ሲሆን፤ ግንኙነቱ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል። 


 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አቶ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ተቋማቱ በጋራ ለመስራት መወሰናቸው ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።   

ተቋማቱ በጋራ ለመተግበር የያዟቸው ግቦች እንዲሳኩ ሁሉን አቀፍ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

 

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም