ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ግብዓት አምራቾች የዘርፉን የግብዓት እጥረት በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ግብዓት አምራቾች የዘርፉን የግብዓት እጥረት በመቅረፍ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ገለጹ።

አገልግሎቱ ከሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግብዓት አምራቾች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን ተደራሽና አስተማማኝ ለማድረግ በርካታ የሪፎርም ስራዎች ተከናውነዋል።

የሀገር ውስጥ ግብዓት አምራቾች ለኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ዝርጋታ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች እጥረትን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በጅምር ደረጃ በሀገር ውስጥ እየተመረተ ያለውን ግብዓት በቀጣይ በሙሉ አቅም በማምረት የቴክኖሎጂ ሽግግር ማረጋገጥና የውጭ ምንዛሪን ማዳን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በቀጣይ አምራቾቹ የተቋሙን የግብዓት ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ለማሟላት ከዚህ በላይ መስራት እንደሚገባቸው ገልጸው ለዚህም አገልግሎቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን በመወከል የተገኙት አቶ ፀሃዬ ይነሱ አምራች ኢንዳስትሪው ተኪ ምርት በማምረት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አንዱ መሆኑን ገልፀው ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓት አምራቾች ጋር የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ አምራቾች መካከል አቶ ዳዊት በላይ እና አቶ ፀሃዬ ይታገሱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግብዓቶችን በመጠቀም የሚያደርገው ድጋፍ አበረታች መሆኑን አንስተዋል።

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓት የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማትን ለማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ የተቋሙን የግብዓት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም