ኢትዮ-ቴሌኮም የአክስዮን ሽያጭ ለካፒታል ገበያ ቀጣይ ጉዞ ፈር ቀዳጅ ተግባር አከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ-ቴሌኮም የአክስዮን ሽያጭ ለካፒታል ገበያ ቀጣይ ጉዞ ፈር ቀዳጅ ተግባር አከናውኗል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮ-ቴሌኮም የአክሲዮን ሽያጭ የካፒታል ገበያ ስርዓትን ማስጀመር ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ጉዞ ፈር ቀዳጅ ተግባር ማከናወኑን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ አስታወቁ።
ኢትዮ-ቴሌኮም ባቀረበው የአስር በመቶ የአክስዮን ሽያጭ 47ሺህ 377 ኢትዮጵያውያን አክስዮኖች መግዛታቸውም ተገልጿል።
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ለህዝብ የቀረበውን የአክስዮን ሽያጭ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም. የኢትዮ-ቴሌኮም አክሲዮን ለሽያጭ ዝግጁ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ማብሰራቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ የአክስዮን ድርሻውን ዝቅተኛው 33 ከፍተኛው 3ሺህ 333 አክሲዮን ለሕዝብ ማቅረቡን አስታውሰዋል።
ከጥቅምት 6 ቀን 2017 እስከ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በጥቅሉ ለ121 ቀናት በዲጂታል መንገድ 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአክሲዮን እጣዎች የተሸጡ ሲሆን በዚህም 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ተናግረዋል።
አሁንም አክሲዮኖችን ለመግዛት ጥያቄዎች መኖራቸውን ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የቀሩ አክሲዮኖችን በተመለከተ በቀጣይ ጊዜያት የምናሳውቅ ይሆናል ብለዋል፡፡
እንደ ስራ አስፈጻሚዋ ገለጻ ኢትዮ-ቴሌኮም አክስዮን ሽያጭ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ማስጀመርና ለገበያው ቀጣይ ውጤታማ ጉዞ ፈር ቀዳጅ ተግባር መሆኑን አስታወቀዋል።
አክስዮን ሽያጩ በዲጂታል መከናወኑ ሰዎች በዲጂታል ገንዘብ እንዲለዋወጡና ባህል እንዲያደርጉት ትልቅ ሚና እንደተጫወተም አንስተዋል።
አካታች ፍትሃዊ ዘላቂነት ያለው የተረጋጋ ኢኮኖሚ ከመገንባት አንጻር የአክስዮን ሽያጩ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮ-ቴሌኮም 2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ግንባር ቀደም ሚና እየተወጣ መሆኑን ስራ አስፈጻሚዋ አመላክተዋል።