የተለያዩ ሀገራት ልዑካን በስፖርት ውድድሩ ለመሳተፍ አዲስ አበባ እየገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ ሀገራት ልዑካን በስፖርት ውድድሩ ለመሳተፍ አዲስ አበባ እየገቡ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2017(ኢዜአ)፡- የደቡብ ሱዳን፣ የሩዋንዳ እና የዩጋንዳ የፖሊስ ስፖርት ልዑካን ቡድኖች በአምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት የስፖርት ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ልዑካኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል አስተዳደር እና ድጋፍ አገልግሎት ዋና መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳያስ እና ሌሎች የተቋሙ አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል።
ቡድኖቹ ወደ ተዘጋጀላቸው የስፖርት መንደር መግባታቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።
የታንዛንያ ፖሊስ የስፖርት ልዑካን ቡድን ትናንት በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።
5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት የስፖርት ውድድር ከሚያዚያ 19 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
ውድድሩ የተዘጋጀው 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታ በዓል ቀንን በማስመልከት ነው።
በስፖርት ውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የጂቡቲ፣ የኬንያ፣ የታንዛኒያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የዩጋንዳ እና የሩዋንዳ የፖሊስ ተቋማት በስድስት የስፖርት አይነቶች ይሳተፋሉ።
አትሌቲክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ዒላማ ተኩስ፣ ቦክስ፣ ዳርት እና እጅ ኳስ ውድድሩ የሚካሄድባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው።
ሌላው የፕሮግራሙ አካል የሆነው በሳይንስ ሙዚየም የሚደረገው ሲምፖዚያም እና አውደ ርዕይ ሲሆን ይህም ከሚያዚያ 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።
የፕሮግራሙ ማጠቃለያም ሚያዚያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በሚደረግ ወታደራዊ ትርዒት እንደሚከናወን የተቋሙ መረጃ ያሳያል።