ቀጥታ፡

በጤናው ዘርፍ ለሚሰጡ አገልግሎቶች ውጤታማነት የሙያ ማሕበራት ሚና ከፍተኛ ነው - ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2017(ኢዜአ)፦ በጤናው ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሙያ ማሕበራት ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የህክምና ላቦራቶሪ ማህበር 30ኛ አመታዊ ጉባኤውን ዛሬ ማካሔድ ጀምሯል።


 

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ በጤናው ዘርፍ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል በርካታ የሪፎርም ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

ከሪፎርም ስራዎቹ መካከልም አዲስ የጤና ፖሊሲ ከማውጣት ጀምሮ አዋጅና መመሪያዎችን ማዘጋጀትና በዘርፉ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ተግባራትን አንስተዋል።

በዋናነትም በዘርፉ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል አዋጅን ወደ ትግበራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

አዋጁ ተግባራዊ ሲደረግም የጤና ባለሙያዎች የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ ከሙያ ማሕበራት ጋር በትብብር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪም የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ ከሙያ ማሕበራት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የላቦራቶሪ አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግና ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር መቅደስ ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ከአጋር ድርጅቶች ጋር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ የህክምና ላቦራቶሪ ማህበር ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አስቴር ፀጋዬ በበኩላቸው፤ ማሕበሩ የላቦራቶሪ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት እየሰራ ነው ብለዋል።

ከዚህ ውስጥም በዘርፉ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማላመድ ስራዎች ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ያሉ የላቦራቶሪዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ገልጸው በአለም አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል።

ማሕበሩ ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ዘርፉን ማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ ውይይቶች እንደሚካሔዱ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም