በመዲናዋ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን፣ የወንጀል መከላከል ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን፣ የወንጀል መከላከል ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች፣ የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዦች፣ የወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊዎች የአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታን በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ገምግመዋል።
በሁሉም ክፍለ-ከተሞች በተካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በተሽከርካሪ ስርቆት፣ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ በሀሰተኛ የብር ኖቶች ዝውውር፣ በበርካታ ሞባይልና ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች ስርቆት፣ በስፖኪዮ፣ በጎማ እና በሌሎች የመኪና መለዋወጫዎች ስርቆት የተጠረጠሩ ግለሰቦች እንዲሁም የ”IMEI” ማጥፊያ ማሽን ተጠቅመው የተሰረቁ ሞባይሎች እንዳይገኙ የሚያደርጉ፣ በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ተጠቅመው ዝርፊያ የሚፈፀሙ እና በርካታ ሽሻ ማስጨሻ ዕቃዎችን ይዘው የተገኙ ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል።
በተለይም በቂርቆስና በቦሌ ክፍለ ከተሞች በቅንጅት በተካሄደ ልዩ ኦፕሬሽን ተደራጅተው በመንግስት መሠረተ ልማቶች ላይ ዝርፊያ የፈፀሙ፣ በሞተር ሳይክል ሞባይል የሚነጥቁ፣ 12 የኤቲኤም ካርድ ከግለሰቦች በማታለል ወስዶ ገንዘብ የዘረፈ ተጠርጣሪ ግለሰብን ጨምሮ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸዉ በምርመራ እየተጣራ መሆኑ ተመላክቷል።
በተካሄደው ኦፕሬሽን የከተማዋ ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ መሆኑንና ወንጀልም በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱ በግምገማው ላይ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማን ፀጥታ እና ደኅንነት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተደረገ ባለው የተቀናጀ ኦፕሬሽን የፀጥታ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር እና የማድረግ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ያደገ መሆኑንም ተነስቷል።
የጋራ ኦፕሬሽኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በኦፕሬሽኑ የተገኙ ውጤችም እየተገመገሙ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።