ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሞሮኮ በወታደራዊ ዘርፍ በትብብር ለመስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፦ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ባሬድ የተመራ ልዑካን ቡድንን ተቀብለው አነጋግረዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በ1955 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ እና ሞሮኮ ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በፓን አፍሪካዊ መንፈስ ለአህጉራዊ አንድነት የጋራ ቁርጠኝነት የታየበት ትብብር እንደሆነ ገልጸዋል።


 

ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ እና በራባት የተካሄደው የከፍተኛ ደረጃ ወታደራዊ ልዑካን ምክክርም ሁለቱ ሀገሮች በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ጉዳዮችን እንዲፈትሹ እድል ፈጥሮላቸው እንደነበርም አውስተዋል።

የሞሮኮ ሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሞሐመድ ባሬድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት ምልክት ናት ብለዋል።

ወታደራዊ ትብብሩ ሀገራቱ ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ለሚኖራቸው አስተዋፅኦ የጎላ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

የመከላከያ ውጪ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ ሁለቱ ሀገራት በየቀጣናቸው ከሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በተጨማሪ በጋራ ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት በትብብር መስራት በሚችሉባት ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውን ጠቁመዋል።


 

ከሞሮኮ ወታደራዊ ተቋማት በቴክኖሎጂ ሽግግር በሳይበር በአየር ኃይልና በባህር ኃይል ኢትዮጵያ ተሞክሮ መውሰድ እንደምትፈልግ አመልክተዋል።

ሁለቱ ሀገራት በቀጣይ የመግባቢያ ስምምነት ይፈራረማሉም ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የአየር ኃይል የባህር ኃይል የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም የሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ውይይቱን ተከትሎ የልዑካን ቡድኑ በሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና በአየር ኃይል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን መጎብኘቱን የሀገር መከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም