በቀጣናው ለዘላቂ ልማት ስጋት የሆኑ ጊዜ የማይሰጡ ችግሮች አፈጣኝ መፍትሄ ይሻሉ - አቶ አሕመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣናው ለዘላቂ ልማት ስጋት የሆኑ ጊዜ የማይሰጡ ችግሮች አፈጣኝ መፍትሄ ይሻሉ - አቶ አሕመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ በቀጣናው ለዘላቂ ልማት ስጋት የሆኑ አንገብጋቢ ችግሮች አፈጣኝ መፍትሄ እንዲያገኙ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ አመለከቱ።
የዓለም ባንክ ግሩፕ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው።
24ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ ከፀደይ ወቅት ሁነቱ ጎን ለጎን ተካሂዷል።
በስብሰባው የገንዘብ ሚኒስትር እና ተሰናባቹ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ሊቀ መንበር አቶ አሕመድ ሽዴ፣ የዓለም ባንክ ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የስብሰባው የጋራ ሊቀ-መንበር አሚት ዳር፣ ቀጣዩ የኢኒሼቲቩ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዝዳንት ንድያሜ ዲዮፕ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በስብሰባው የኢትዮጵያ የኢኒሼቲቩ ሊቀ-መንበርነት በይፋ ተጠናቋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ እንደገለጹት ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋትና ሌሎች በቀጣናው ዘላቂ ልማት ራዕይ ላይ ስጋት የደቀኑ ጊዜ የማይሰጡ ፈተናዎች በአፋጣኝ እንዲፈቱ የጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል።
ቀጣናው በነዚህ ፈተናዎች ውስጥ እንኳን ሆኖ ሁለት ሶስተኛ ሀገራት በዘንድሮው የፈረንጆች ዓመት ከአምስት በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገባቸውን አመልክተዋል።
ይህ መልካም ዜና በአፍሪካ ቀንድ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ያለውን አቅም በግልጽ የሚያመላከት ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።
የሶማሊያ የፋይናንስ ሚኒስትር ቢሂ ኢማን ኤጌህ የኢኒሼቲቩን ሊቀ-መንበርነት ከአቶ አሕመድ ሽዴ ተረክበዋል።
አቶ አሕመድ አዲሱ ሊቀመንበር የኢኒሼቲቩን ስራ ወደ ፊት ይበልጥ እንደሚያራምዱት እምነታቸው እንደሆነ ገልጸው የቀጣናውን የጋራ ግቦችን ለማሳካት በጋራ እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል።
24ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቀጣናው የማይበገር አቅም ለመገንባት፣ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥና ቀጣይነት ያለው አጋርነት መፍጠር የሚያስችል መድረክ እንደነበር ተገልጿል።
ባለድርሻ አካላት ለቀጣናው ትስስር እና ልማት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መናገራቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ እ.አ.አ በ2019 በዓለም ባንክ፣ በአውሮፓ ህብረትና፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረተ ቀጣናዊ የትብብር ማዕቀፍ ነው።
ኢኒሼቲቩ ንግድ እና ኢኮኖሚን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያለውን ቀጣናዊ ትብብር ማጠናከርን ዋነኛ አላማው አድርጓል።