ቀጥታ፡

የኩዌት ፈንድ ለኢትዮጵያ መሰረተ ልማት ግንባታ እና ለልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ የኩዌት ፈንድ የመሰረተ ልማት ግንባታ እና የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታወቀ።

የዓለም ባንክ ግሩፕ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ መካሄዱን ቀጥሏል።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከኩዌት ፈንድ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ዋሊድ አል-ባሃር ጋር ተወያይተዋል።


 

ሚኒስትሩ ለዳይሬክተር ጀነራሉ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የልማት ትኩረቶች እና የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ጅምር ውጤቶችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ሪፎርሙ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ገበያ መር ስርዓት የሚያሸጋግር እና የግሉ ዘርፍ በሀገሪቱ ኢንቨስትመንት ላይ ያለውን ተሳትፎ የሚያሳድግ መሆኑን አመልክተዋል።

የኩዌት ፈንድ መሰረተ ልማትን ጨምሮ ለተመረጡ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በተለይም የመሰረተ ልማት ግንባታ ምርታማነት እንደሚያሳድግ እና የኢትዮጵያን ሙሉ የኢኮኖሚ አቅም መጠቀም እንደሚያስችል ነው ያስረዱት።

የኩዌት ፈንድ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ዋሊድ አል-ባሃር በበኩላቸው ፈንዱ የኢትዮጵያን ቁልፍ የመሰረተ ልማትና ወሳኝ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን አመልክተዋል።

ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው የኢትዮጵያ እና ኩዌትን አጋርነት ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በተጨማሪም ፈንዱ የኢትዮጵያን እድገት እና የልማት ህልሞች የሚያሳኩ ስትራቴጂካዊ እና ውጤታማ ፕሮጀክቶችንም እንደሚደግፍም ተገልጿል።

ከሚያዚያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የዓለም ባንክ ግሩፕ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ ነገ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም