በደሴ ከተማ ለ50ሺህ ዜጎች የሚሆን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ይገነባሉ - አስተዳደሩ - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ከተማ ለ50ሺህ ዜጎች የሚሆን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ይገነባሉ - አስተዳደሩ
ደሴ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ በደሴ ከተማ አስተዳደር በሁለት ዙር ለ50 ሺህ ዜጎች የሚሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንደሚገነቡ የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለፁ፡፡
አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በደሴ ከተማ እየተስፋፋ ከመጣው የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በከተማው የህዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መጥቷል።
በዚህም ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤት እጥረትና በቤት ኪራይ ውድነት እንዲሰቃይ ማድረጉንም ገልጸዋል።
ይህን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ በሁለት ዙር 50ሺህ ዜጎችን በጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ ቤቶቹ የሚገነቡበትን ቦታ የማመቻቸት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፣ በመጀመሪያው ዙር 28ሺህ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
በመሆኑም የከተማዋ ነዋሪዎች በሚሰሩበት መስሪያ ቤትና በሚኖሩበት ቀበሌ ከሚያዚያ 20 እስከ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ መደራጀት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ህበረተሰቡ በአቅሙ ልክ ከባለ አንድ መኝታ ቤት እስከ ባለ ሦስት መኝታ ቤት መመዝገብ እንደሚችል ጠቁመው፣ ለባለ አንድ መኝታ 72፣ ለባለ ሁለት መኝታ 54 እና ለባለ ሦስት መኝታ ቤት 42 ሰው በመሆን መደራጀት ይችላሉ ብሏል።
የመኖሪያ ቤት ግንባታው የከተማውን የወደፊት የልማት አቅም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸው የቤቶቹ ሕንጻዎች ባለአምስት ወለል ሲሆኑ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትና መሰረተ ልማት እንደሚሟላላቸው ተናግረዋል።
የተደራጁ ሰዎችን መረጃ እስከ መስከረም ወር 2018 ዓ.ም የማጣራት ሥራ እንደሚሰራ ገልጸው፣ ሥራውን ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በብድር ጭምር ለማስተሳሰር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ለግንባታ የሚያስፈልገው መሬት ከ70 በመቶ በላይ መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ በከተማው የልማት ተነሺዎችም መልሰው እንዲቋቋሙ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር ተመቻችቷል ብለዋል።
በሁለተኛ ዙር ግንባታም 22ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የቤቶቹ ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ገልጸዋል።
የቤት ልማት ሥራው ስኬታማ እንዲሆን ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ህብረተሰቡ ሰላሙን ለመጠበቅና ለማጽናት ከመንግስት ጎን በመሆን የጀመራቸውን ሥራዎች ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል፡፡