የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ለአፍሪካ ህብረት የድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲደረግ ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ለአፍሪካ ህብረት የድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲደረግ ጠየቁ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡ -የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) አባል ሀገራት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ለአፍሪካ የድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ(አውሶም) ጠንካራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ።
የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) የሰላም አስከባሪ ኃይል አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሀገራት አስቸኳይ ጉባኤ ዛሬ በዩጋንዳ ካምፓላ ተጀምሯል።
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በጉባኤው ባደረጉት ንግግር የአውሶም ተልዕኮን የሚያግዝ ድጋፍ መዘርጋት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የቀጣናዊ ተቋሙ አባል ሀገራት ሽብርተኞችን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ሎጅስቲክስን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
ለሶማሊያ የጸረ-ሽብር ዘመቻ የተቀናጀ እና በበቂ ሁኔታ በፋይናንስ መደገፍ የሚያስችል አካሄድ መከተል ይገባል ብለዋል።
የሶማሊያ መንግስት እና የፀጥታ ኃይሎች አልሻባብን በመዋጋት ላመጡትን ለውጥ እውቅና የሰጡት ዋና ፀሐፊው የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠል ዘላቂ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ኢጋድ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን በአባል ሀገራት ዘላቂ ሰላም፣ ደህንነት እና ልማት እንዲሰፍን በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ነው ብለዋል ዋና ፀሐፊው።
ኢጋድ ሰላሟ የተረጋገጠ እና ደህንነቷ የተጠበቀ ሶማሊያ ለመፍጠር የተያዘው ራዕይ እውን እንዲሆን ከሀገሪቷ ጎን በመቆም በትብብር እንደሚሰራ መግለጻቸቸውን ኢዜአ ከኢጋድ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
አስቸኳይ ጉባኤው የፋይናንስ ማዕቀፎች እና ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀትን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ በሶማሊያ የሚኖረውን አጠቃላይ ቆይታ ላይ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢጋድ አባል ሀገራት፣ የቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም አጋሮች ተገኝተዋል።